Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፡ ከተሞችን መስራት

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 67

ጊዜ እንደ ወንዝ ይፈሳል፤ ታሪክ ደግሞ በዘመናት ገፆች ላይ የማይፋቅ አሻራውን ያትማል።

ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት አንስቶ ወደ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዋዜማ ስንሸጋገር፣ የኢትዮጵያ ከተሞች የፃፉት ታሪክ የድንጋይና የሲሚንቶ ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የውበት፣ የከፍታና ዳግም የመወለድ የሥልጣኔ ትርክት ነው። እነዚህ ያለፉት አምስት ዓመታት የከተሜነት ትርጉም ከስር መሰረቱ የተቀየረባቸው፣ መዲናችን አዲስ አበባና የክልል ከተሞች ከድካምና ከእርጅና መንፈስ ተላቀው እንደ አዲስ የተዋቡባቸው ደማቅ የለውጥ ገፆች ናቸው።

ከተሜነት ከጥንት ጀምሮ የስልጣኔና የዕድገት መገለጫ ነው። የሱሜርያን ኡሩክ፣ የጥንቷ አቴንስ፣ ታላቋ ሮምና ባግዳድ የሥልጣኔ ማዕከል እንደነበሩት ሁሉ፣ መንግስት ከተሜነትን ከቴክኖሎጂ፣ ከዘመናዊነትና ከዕውቀት ጋር በማስተሳሰር ከተሞቻችንን የዕድገት ኮሪዶር የማድረግ ራዕይ ሰንቆ ተነስቷል። ባለፉት አምስት ዓመታት ከተሜነት ማለት በምቾት መኖር ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚን የማሳደግ፣ ለዜጎች ምቹ መኖርያ ማድረግ፣ ሥርዓትን የማስፈንና የሰዎችን አብሮነት የማጠናከር ምሰሶ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስናልፍ የምንመለከተው የትላንቱን ስርዓት አልባ ፣ ትርምስና ጥግግት የፅዳት ጉድለት ሳይሆን፣ ነፍስ የዘራውን ሰፊና ውብ የዝመናና የጥበብ መሰናሰልን ነው። ይህ ታላቅ ስራ መዲናዋን እንደ ስሟ አዲስና ውብ አበባ እንድትሆን፣ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ እጅግ ምቹ እንድትሆን አድርጓታል። ሲመሽ በመንገዶቿ ዳርቻ የሚፈነጥቁት ደማቅና ሕብረ-ቀለም የሌሊት መብራቶች ከተማዋን የብርሃን ድንኳን አስመስለዋታል። የተንጣለሉ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የብስክሌትና ለእግረኛ ምቹ የሆኑ መንገዶች የነዋሪውን ሥነ-ልቦና ከፍ አድርገውታል። ያረጁና የተጎሳቆሉ ሰፈሮች በአዲስና ውብ ስነውበታዊ አካታች ልማት ሲተኩ፣ የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ፣ የጎርፍና የፍሳሽ ማስወገጃ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ተችሏል።

 

 

ከዚህም ባሻገር፣ ከቆሻሻ ማራገፊያነት አልፈው ለዘመናት የተረሱት የከተማችን ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ላይ የውበትና የመዝናኛ ማዕከል ሆነው ተመልሰዋል። የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የተፈጥሮን ፀጋ ወደ ከተማው ልብ በማምጣት፣ ከተማዋ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እያስቻሏት ይገኛሉ። እነዚህ የመዝናኛና የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ከመንገድ፣ ውሃና መብራት አቅርቦት እኩል የብልፅግናችን መገለጫዎች ሆነዋል።

ይህ የክትመትና የውበት ማዕበል በመዲናዋ ብቻ የተገታ አልነበረም። የክልል ከተሞችም የዚህ አዲስ የከተሜነት ሽግግር አካል በመሆን የነዋሪዎቻቸውን ኑሮ የሚያቀሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አስተናግደዋል። ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭትን ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ፣ በየክልሉ ያሉ ከተሞች አዳዲስና ሰፊ መንገዶችን፣ ዘመናዊ መናፈሻዎችንና የህዝብ መገልገያዎችን በመገንባት ነዋሪው በኩራት የሚኖርባቸው ማዕከላት ሆነዋል። ከተሜነት የህንፃዎች ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎች ተግባብቶና ተዋህዶ የመኖር ጥበብ መሆኑ በክልል ከተሞቻችንም ጭምር ታይቷል።

የአምስት አመት ቅኝታችን እነሆ ዛሬ ጀምሯል፡፡ አብረን እንዝለቅ!!