Search

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለማቋቋም ያስችላል

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 65

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት እያካሄደ ነው።

ይህ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የአጥኚ ቡድኑ እና የሕጉ አርቃቂ ኮሚቴ ሰብሳቢ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ መሐመድ አህመድ አዋጁን ለማሻሻል ሰፊ ጥናት መደረጉን ጠቁመው፣ በጥናት ሂደቱም የበርካታ ሀገራትን ተሞክሮ በመነሻነት መመልከታቸውን በዝርዝር አብራርተዋል።

ይህ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለማቋቋም፣ የፍርድ ቤቶችን የሥራ ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት እና ራሱን የቻለ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።

በተጨማሪም በሪፖርቱ አቀራረብ ወቅት እንደተመለከተው፤ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የውርስ ማጣራትና የሀብት ክፍፍል ጉዳዮች በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ በግልጽ የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ / እፀገነት መንግሥቱ በበኩላቸው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የፍትህ ሥርዓት በማሻሻል ረገድ እጅግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው፣ አሁን እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ውይይት መድረክም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተጨማሪ ጠቃሚ ግብዓቶችን በስፋት ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

በዚሁ የሕዝብ ውይይት መድረክ ላይ የተገኙ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ ሊካተቱና ሊስተካከሉ ይገባል ያሏቸውን ገንቢ ሐሳቦች ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

አሁን ለውይይት የቀረበው ይህ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ 25 ዓመታት በላይ ረጅም ጊዜ ሳይሻሻል የቆየውን ነባሩን የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ሙሉ በሙሉ የሚተካ ይሆናል።