የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) በዛሬው ዕለት ካስመረቃቸው 1 ሺህ 387 ተማሪዎች መካከል የኤሌክትሪካል ፓወር ኤንድ ኮንትሮል ኢንጅነሪንግ ተማሪዋ ሩት አባተ የዓመቱ ኮከብ ተማሪ በመሆን የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።
ሩት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ከወሰደቻቸው 60 ኮርሶች መካከል 47ቱን 'A+' እንዲሁም 13ቱን 'A' በማምጣት ሙሉ 4.00 (አራት ነጥብ) ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ (Very Great Distinction) ተመርቃለች።

በአዳማ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ሩት፣ ለዚህ ውጤት የበቃችው ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ባደረገችው ተከታታይ ጥረትና ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ ለትምህርቷ ልዩ ትኩረት በመስጠቷ እንደሆነ ገልጻለች።
ለስኬቷ የቤተሰቦቿ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የጠቀሰችው ሩት፣ በተለይም አባቷ የቅርብ አማካሪና አስጠኝ በመሆን፣ እናቷ ደግሞ የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ ለውጤቷ መሳካት ትልቅ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጻለች።
ሴቶች የመማር ዕድል ካገኙ ማህበራዊ ጫናዎችን አልፈው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ሩት ትናገራለች።
በቀጣይም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የመቀጠል እቅድ ያላት ሲሆን፣ “በኢነርጂውና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለሀገሬ ጠቃሚና ችግር ፈቺ ባለሙያ ለመሆን እተጋለሁ” ስትል ምኞቷን ገልጻለች።