Search

2.3 ትሪሊዮን ብር ለላቀ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 50

 

የላቀ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማምጣትና የተጀመሩ ሀገራዊ የለውጥ ጥረቶችን ለማሳካት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 56 መደበኛ ስብሰባ 2019 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት በጀት 2.3 ትሪሊዮን ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ረቂቅ ሰነዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

ይህ የተመደበው በጀት ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገቡት ስኬቶች መነሻነት፣ እንዲሁም የአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ አካል በሆነው የልማትና ኢንቨስትመንት ግቦች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው  ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (/) እንደገለጹት፣ ይህ የበጀት መጠን ማደግ መንግሥት ካለው የማስፈጸም አቅምና የፊስካል ፖሊሲ ጥንካሬ ጋር የተያያዘ ነው።

መንግሥት በአንድ በኩል ያለው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ያሳየ ሲሆን፣ ይህም ገቢ ከታክስ የሚሰበስበውን፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ብድሮችና እርዳታዎች፣ እንዲሁም በኤክስፖርት እና ከዲያስፖራ የሚገኘውን ገቢ እንደሚጨምር አስገንዝበዋል።

ባለፉት ጊዜያት የተጀመሩ እና የተጠናቀቁ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን አመላክተዋል። በዚህ መነሻነትም ካለፈው በተሻለ 2019 በጀትም ለተለያዩ ፕሮጀክቶችና ማህበራዊ አገልግሎቶች ሊውል የሚችል በጀት መሆኑን ጠቅሰዋል።

/ ቆስጠንጢኖስ አያይዘውም 2019 በጀት 2018 ብልጫ ማሳየቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት እና በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ሰፊ መሻሻሎችን ለማምጣት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰዋል። ሆኖም የታሰበውን የኢኮኖሚ እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ሀገራችን ያላትን የሰው ኃይል፣ የውኃ፣ የግብርና እና የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርንና ሕገወጥ ንግድን በቁርጠኝነት መግታት እንደሚገባ / ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል።

ለዚህም የሲቪል ማህበረሰቡ እና የሚዲያ ተቋማት በንቃት በመሳተፍ ሕገወጥ አሰራሮችን እንዲያጋልጡና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ የዘንድሮው 2.3 ትሪሊዮን ብር ረቂቅ በጀት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅምና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው ብለዋል።