ጽንፈኛ ቡድኑ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይሳካ ያደረገው ሙከራ በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ከንቱ ሕልም ሆኖ መቅረቱን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል አቶ ጣሂር መሐመድ ገለጹ።
አቶ ጣሂር መሐመድ በምርጫው እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ውይይት እንዳሉት፣ የአማራ ክልል ሕዝብ በነጻነት የራሱን መሪዎች እንዳይመርጥ ጽንፈኛው ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጭምር በመቀናጀት ምርጫውን የማደናቀፍ ተግባራት ላይ ተጠምዶ ቆይቷል።
ጽንፈኛው ቡድን መራጩን ሕዝብ በዚህ ምርጫ ትሳተፍና፣ ይሄን ታደርግና የሚሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎች ጭምር በመጠቀም አደገኛ ቅስቀሳዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በመሰል እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ ዋጋ ሲከፍል መቆየቱን ጠቅሰዋል።
እንዲያም ሆኖ የአማራ ክልል ሕዝብ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ በመስጠት ምርጫውን እንዲሳካ አድርጓል ያሉት አቶ ጣሂር፤ ለዚህ በሳል ውሳኔ ሕዝቡ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሕዝቡ ወጥቼ እመርጣለሁ፤ የምፈልገው መደበኛ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር ነው በሚል መርሕ በመመራት ምርጫውን ማሳካቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻጻሪው የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የአማራን ሕዝብ እንደማይገልጸው ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋል።
በሕዝቡ ድምፅ የሚመሰረተው መንግሥት ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ ያመላከተ ነው ያሉት አቶ ጣሂር፤ ሕዝቡ በሰላም ዙሪያ በሚሰሩ ሥራዎች ተባባሪና ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየበት ምርጫ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአማራ ክልል የተካሄደው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ሚሊሻዎች በየደራጃው ካሉ አመራር ጋር በቅንጅት ያከናወኑት ተግባር ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ይሄ ውጤት ደግሞ በመንግሥት እና በመደበኛ ሥርዓት ሕዝቡ እንዲተማመን ያስቻለ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ጣሂር ገለጻ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋ የኃይል አሰላለፍ ሕዝብንም ሀገርንም ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሕዝቡ በዚህ ላይ ግንዛቤ ጨብጦ ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እየሠራ ነው።
"ጥያቄዎች የሚመለሱት በኃይል ነው" የሚል አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት አውድ መፍጠር ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት የሰላም ጥሪ አቅርቦ በሩን ክፍት ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን አመልክተው፣ ይሄ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።