Search

"የኢትዮጵያ ሕዝብ የምክክር ጉባኤ" ሐምሌ 8 በይፋ ይጀመራል፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 57

በኢትዮጵያ  በሂደት ላይ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ሀገራችን ወደ አዲስ የፖለቲካ የታሪክ ምዕራፍ የምትሻገርበት ወሳኝ ድልድይ እየተገነባ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በሀገራችን ስር የሰደዱና ለዘመናት የቆዩ የቅራኔ ምንጮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመፍታት ታሪካዊ ኃላፊነት ተረክቦ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ዋነኛ ግቡም በፖለቲካው ሳቢያ  የሚስተዋሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ነው። ይህም ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ ማኅበራዊ መተማመንን ለማደስ እና የሀገርን አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያለመ ነው።

ኮሚሽኑኢትዮጵያ እየመከረች ነው!” በሚል መሪ ቃል እያከናወነ ያለው ተግባር፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ ካለበት የድሮ የፖለቲካ ባህል ወጥተን በጋራ የምናሸንፍበትን አዲስ መንገድ እየቀየሰ ይገኛል።

ይህ ታሪካዊ ሂደት የፖለቲካ ልሂቃን መድረክ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ኅብረተሰብ ድምፅ የሚሰማበት ዕውነተኛ መድረክ ነው።

የምክክር ኮሚሽኑ የሀገራችንን 93 በመቶ መልክዓ ምድራዊ ወሰን መሸፈን ችሏል። 12 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 1 ሺህ 234 በላይ ወረዳዎች ተወካዮቻቸውን ለይተዋል። ለአጠቃላይ ምክክሩ የሚሆኑ የአጀንዳ ሐሳቦችንም ለኮሚሽኑ በይፋ ማስረከባቸውም ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ምክክሩን ሙሉ በሙሉ አካታች ለማድረግ 1 ሺህ 300 ወረዳዎችን፣ 13 ሺህ ቀበሌዎችን እና 91 ሺህ በላይ ጎጦችን ያገናዘበ ዝርዝር መዋቅራዊ ሥልተ-ቀመር ነድፎ በተግባር ተርጉሟል።

የኮሚሽኑ አሳታፊነት በማኅበረሰብ ክፍሎች ስብጥር እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ላይ በጉልህ ይንጸባረቃል።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ የሴቶች ተሳትፎ 45 በመቶ በላይ እንዲሆን በልዩ ትኩረት ተሠርቷል። በፌዴራል ደረጃ 900 የሚጠጉ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 220 የሚሆኑት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ 51 የመንግሥት እና 5 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 1 ሺህ 200 የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ኃላፊዎችና የሥራ መሪዎች በሂደቱ ተሳትፈዋል።

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ከዓረብ ኤምሬቶች፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከሰሜን አሜሪካ የተውጣጡ የዳያስፖራ አባላትንም ማካተት ተችሏል።

አሁን የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የአጀንዳ ቀረፃ ዝግጅት ማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ታሪካዊው "የኢትዮጵያ ሕዝብ የምክክር ጉባኤ" ሐምሌ 8 ቀን 2018 . በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ ይጀመራል።