Search

ከሐምሌ 8 ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 45

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋና ጉጉት የሚጠብቀው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በይፋ መካሄድ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የኮሚሽነሮች ምክር ቤት ጉባኤው ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ እንዲካሄድ የወሰነ ሲሆን፣ ይህ ታሪካዊ መድረክ ቢያንስ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት እንደሚቆይ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች የሆነ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ ከገባች አራት ዓመታት መቆጠራቸውን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ ዋናው ጉባኤ የሚያደርሱ እጅግ መሠረታዊ ተግባራት በስኬት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሂደቱ ተዓማኒነት ያለው፣ ግልጽ፣ ገለልተኛና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ በተደረገው ያላሰለሰ ጥረት በመላ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል በ1ሺህ 234ቱ ውስጥ የአጀንዳ ማሰባሰብና የውይይት ተግባራትን ማከናወን የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የ93 በመቶ መልክዓ ምድራዊ ሽፋን እንዳለው ተብራርቷል።

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ፤ በአስራ ሁለት ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የፌዴራል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል።

ከዚህም በተጨማሪ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራዎች) በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት ፍሬያማ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት አካባቢዎቹ ለዋናው ጉባኤ የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች በንቃት በመምረጥ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምንሻውን ያህል ወደፊት እንዳትራመድ ያደረጓት ስር የሰደዱ ቋጠሮዎችና ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር ብቻ መሆኑን ሕዝቡ ተገንዝቦ ላሳየው ከፍተኛ የባለቤትነት መንፈስ ዋና ኮሚሽነሩ ጥልቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለዚህ ተስፋ ሰጭ እና ታሪካዊ ምዕራፍ መድረስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነትና ትጋት ላበረከቱት ታሪክ የማይዘነጋው አስተዋጽኦ ዕውቅና የሰጡት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በሂደቱ ያጋጠሙ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችንና ፈተናዎችን በጋራና በጥበብ በማለፍ አሁን ወደ ዋናው ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉን አረጋግጠዋል።