Search

ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ችግኞች ለነገዋ ኢትዮጵያ

ቅዳሜ ሰኔ 06, 2018 53

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) “አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከልየሚለው ወቅታዊ ጥሪ እና ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው፣ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ ወደ ላቀ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ክስተት ነው።

ይህ ግዙፍ ዝግጅት ሀገራችን  ካላት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቁርጠኝነት ባሻገር፣ ባለፉት ዓመታት የገነባችውን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ፣ የሕዝብ ንቅናቄ እና የችግኝ ማፍላት አቅም በተግባር የሚያሳይ ነው።

ዘንድሮ ለተከላ የተዘጋጁት እነዚህ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች  የዛፍ ተከላ ብቻ  ሳይሆኑ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም እና የሀገራችንን የደን ሽፋን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ ግስጋሴ አካል ናቸው።

ኢትዮጵያ 2011 . የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄን በይፋ ከጀመረችበት ጊዜ አንሥቶ በአንድ ጀምበር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ መሆን የቻለችበትን ታላቅ ታሪክ አስመዝግባለች።

ካለፉት ዓመታት የተገኘው ትልቁ ስኬት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን፣ የተተከሉትን ዕፅዋት የፅድቅ መጠን በአስተማማኝ ሁኔታ ከፍ ለማድረግ የተዘረጋው የክትትል ሥርዓት እና በሕብረተሰቡ ዘንድ የሰረፀው የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ነው። ይህ ጠንካራ ተሞክሮ እና ልምድ ለዘንድሮው 8 ቢሊዮን ችግኞች ግዙፍ ዕቅድ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

መርሐ ግብሩ የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባለፈ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እጅግ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው።

ባለፉት ዓመታት ከተተከሉ አጠቃላይ ችግኞች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ የመሳሰሉ የፍራፍሬ ተክሎች ሲሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ  በመሆናቸው መርሐ ግብሩን የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለአረንጓዴ ሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ሚና የላቀ ያደርገዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ አብዮት በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ለጎረቤት ሀገራት ችግኝ የመትከል ተሞክሮዎችን  በማካፈል ቀጣናዊ ትስስርን እና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲን በተግባር ያሳየ ታላቅ አህጉራዊ ሥራ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስን ጨምሮ የተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ እና በምሥራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት የመቋቋም አቅምን ለመገንባት የሚጫወተው ሚናም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

በመሆኑም የዘንድሮውን 8 ቢሊዮን ችግኞች በታቀደለት መንገድ ማሳካት የሀገራችን የደን ሽፋን ከማሳደጉም በላይ ለቀጣዩ ትውልድ ለምለም፣ ውብ እና የተደላደለች ሀገርን ለማውረስ ዋስትና ስለሚሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ ጥሪውን ተቀብሎ በንቅናቄው ላይ የራሱን ዐሻራ ማሳረፍ ይጠበቅበታል።

በሔዋን ጌታቸው