በአየር ንብረት ለውጥ እና በበረሃማነት ስጋት ውስጥ ለምትገኘው መሬት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የተጀመረው የኢትዮጵያ "አረንጓዴ ዐሻራ" መርሐ ግብር በአሁኑ ወቅት የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትኩረት ማዕከል ሆኗል።
ይህ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የደን ልማት ሥራ የአካባቢ መራቆትን ከመግታት ባለፈ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተግባር የተፈተነ እና ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ስኬታማ ሞዴል ሆኖ ቀርቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በየዓመቱ የሚከናወነውን የችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ዘመቻ በቅርበት ሲከታተሉ ቆይተዋል።
በዚህም ተቋማቱ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በአንድ ዓላማ ማሰለፍ መቻሏን እና በጥቂቴ ዓመታት ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከልና ማፅደቅ መቻሏን እንደ ትልቅ የልምድ ምንጭ እየወሰዱ ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን፣ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የብዝኃ ሕይወት መጥፋት እና ብክለት ያካተተውን ሦስትዮሽ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ለመቅረፍ የሚያስችል ጠቃሚ ሞዴል አድርጎ በግልጽ አስቀምጧል።
በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን የኢትዮጵያን ጠንካራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ማድነቃቸው ይታወሳል።
የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ቀልብ ከሳቡት መካከል መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ከምግብ ዋስትና እና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ያለው ጥብቅ ትስስር መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ውጤታማ የልማት ሥራ ድርጅትቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በአግሪኮላ ሜዳሊያ ሸልሟል።
በሮም በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት የተበረከተው ይህ ሜዳሊያ ተቋሙ የሚሰጠው ከፍተኛው የክብር ሽልማት ነው።
ሽልማቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና፣ በግብርና ምርታማነት እና በዘላቂ የልማት ስራዎች ላከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት እውቅና ለመስጠት የተበረከተ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
የዓለም ባንክ እና ሌሎች የልማት አጋሮችም ይህንን አካሄድ በማድነቅ ለተለያዩ አካባቢያዊና አሕጉራዊ ፕሮጀክቶች እንደ ማሳያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
ይህ ታላቅ የሕዝብ ንቅናቄ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎችንና የአየር ንብረት ድርድር ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ እንደ ትልቅ ማሳያ መወሰድ ጀምሯል።
በሃና ምንዳሁን