የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን መሪነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እና ተወዳዳሪነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ እየገነባ ያለው ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገራችንን ገጽታ የሚቀይር ታሪካዊ ሜጋ ፕሮጀክት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ጥር ወር ይፋ ያደረጉት ይህ 12.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እና 3.73 ሚሊዮን ቶን ጭነት (ካርጎ) የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ እ.አ.አ በ2029 ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚጀምር ሲሆን፣ ለዚህም የመሬት ጠረጋ እና የቁፋሮ ሥራዎች 610 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦላቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የዚህ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ዘርፈ-ብዙ ነው። ፕሮጀክቱ ወደ ቢሾፍቱ ያመራበት ዋነኛ ምክንያት ከመሬት ከፍታ ጋር የተያያዙ ቴክኒካዊ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በማሰብ ነው።
የአሁኑ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ላይ በመገኘቱ፣ አውሮፕላኖች በተለይም ወደ ሰሜን አሜሪካ ለሚያደርጉት የረጅም ርቀት በረራ የነዳጅ እና የጭነት መጠናቸውን ለመቀነስ ይገደዱ ነበር።
በአንፃሩ የቢሾፍቱው ፕሮጀክት 1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ሙሉ የነዳጅ እና የካርጎ አቅማቸውን በመያዝ ያለምንም ተጨማሪ የቴክኒክ ማቆሚያ በቀጥታ እንዲበርሩ ያስችላቸዋል።
ይህም የበረራ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም ባሻገር አየር መንገዳችን በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት በእጅጉ ያሳድገዋል።
ከበረራ አገልግሎት ባሻገር ፕሮጀክቱ "አይሮትሮፖሊስ" (Aerotropolis) ወይም የአቪዬሽን ከተማ ጽንሰ-ሐሳብን ያነገበ ነው።
በውስጡም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የንግድ ማዕከላትን እና ዘመናዊ የሎጂስቲክስ መዋቅሮችን ያካተተ ነው።
ይህ ግዙፍ መዋቅር መንግሥት አሁን ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተገበረ ካለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጋር በቀጥታ የሚናበብ ነው።
በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩም በላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና በማረጋገጥ የምሥራቅ አፍሪካ ዋነኛ የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን ሰፊ በር ይከፍታል።
ይህ ስትራቴጂያዊ የኢንቨስትመንት እርምጃ የዓለም ኃያላን ሀገራትን ቀልብ ጭምር መሳብ ችሏል።
አየር መንገዱ የግንባታውን 30 በመቶ ወጪ በራሱ አቅም ሲሸፍን፣ ቀሪው 70 በመቶ በአፍሪካ ልማት ባንክ መሪነት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰባሰብ ነው።
የፕሮጀክቱ ግዝፈት እና አዋጭነት በተለይም በአሜሪካ መንግሥት እና በታላላቅ የንግድ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።
በዓረብ ሀገራት እና በአፍሪካ ጉዳዮች የሜሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ሀገራቸው ለዚህ ፕሮጀክት ያላትን አጋርነት አረጋግጠዋል።
ይህ ፍላጎት አየር መንገዳችን ከግዙፉ የአሜሪካ የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ጋር ካለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት ጋር ቀጥተኛ ትሥሥር አለው።
የገዛቸው እና በትዕዛዝ ላይ ያሉ ከ100 በላይ አውሮፕላኖች ወደ ሰሜን አሜሪካ በቀጥታ ለመብረር የቢሾፍቱ ዝቅተኛ ከፍታ እጅግ ወሳኝ መሆኑን የቦይንግ አመራሮች በግልጽ ደግፈውታል።
ይህ ዘመን ተሻጋሪ ሜጋ ፕሮጀክት ሀገራችን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን የበላይነት የምታረጋግጥበት ብቻ ሳይሆን፣ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን በማፋጠን እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትሥሥሯን በማስፋት አዲስ ታሪክ የምትጽፍበት ደማቅ ዐሻራ ነው።
በለሚ ታደሰ