በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ በተለያዩ ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአቡዳቢ ለሚገኙ የአፍሪካ አምባሳደሮች ሰፊ ገለጻ ሰጥቷል።
ማብራሪያውን የሰጡት በአቡዳቢ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ገለጻው በዋናነት በቅርቡ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላ ምርጫ፣ በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ በኮፕ32 (COP32) የአየር ንብረት ጉባኤ ዝግጅት እና በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
አምባሳደር ጀማል ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የምርጫ ሂደት መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርጫውን የታዘቡት የአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ ታዛቢ ልዑካንም ሂደቱ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና በአግባቡ የተመራ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም በ12 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ስላለውና በአፍሪካ አህጉር ትልቁ የአውሮፕላን ማረፊያ ልማት ፕሮጀክት ስለሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ሂደት እንዲሁም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) በሊቀመንበርነት እንድታስተናግድ ስለመመረጧ ለዲፕሎማቶቹ ሰፊ መረጃ አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተም የህወኃት አክራሪ ቡድኖች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገ-ወጥ መንገድ ማፍረሳቸውን ያነሱት አምባሳደሩ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የውጭ ተዋናዮች እጅ እንዳለበትና ሁኔታውን እያባባሱት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ይህንን ድርጊት እንዲያወግዙና ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን ለምትከተለው ቁርጠኝነት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የአፍሪካ አምባሳደሮች ኢትዮጵያ ስኬታማና ሰላማዊ ብሔራዊ ምርጫ በማካሄዷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ትልቁን ዘመናዊ ኤርፖርት እየገነባች መሆኑን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የኮፕ32 የአየር ንብረት ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧን አድንቀዋል።
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጄክቶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የመላው አፍሪካ ኩራትና ሀብት መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደሮቹ፣ ለፕሮጄክቶቹ ስኬታማነትና ፍጻሜ ማግኘት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በጋራ ለመሥራት ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።