ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ከመንግሥት አቅም በላይ የሆኑ ማኅበረሰባዊ ችግሮችን በመፍታት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እያበረከቱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለው በጀት ብቻ ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም፤ ይልቁንም የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ጉልበት፣ ሀብት እና ዕውቀት ሲቀናጅ በርካታ አገራዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል። የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ከበጀትና ከልማት በላይ ማኅበረሰቡን የሚያስተሳስሩ፣ የሚያዋህዱና በመልካምነት አሻራ እንድናሳርፍ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከሚከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባትና መጠገን፡ አምና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ (በወልቂጤ፣ ስልጤ፣ ወራቤ፣ ሀዲያ እና ከምባታ) የተጀመረውና ዘንድሮ ደግሞ በወሊሶ እየተከናወነ ያለው የቤት ግንባታ ተስፋፍቶ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች፡ አገር በቀል ዛፎችንና የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል እንዲሁም የባሕር ዛፍ ተከላን መቀነስ።
መሠረተ ልማቶችን ማሟላት፡ የገጠር መንገዶችን፣ መለስተኛ ድልድዮችን፣ ጤና ኬላዎችን፣ ፋርማሲዎችን እና መዋዕለ ሕፃናትን በሕዝብ አቅም መገንባት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ማሳያ ካነሷቸው ታላላቅ ስኬቶች መካከል ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት በሕዝብ ትብብር የተገነቡት 35 ሺህ መዋዕለ ሕፃናት ይገኙበታል። ይህ ስኬት መንግሥት አቅዶ ቢሆን ኖሮ በርካታ ዓመታትን ይፈጅ እንደነበር ጠቁመዋል።
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ4 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ዕውቀትን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና አብሮ መዋልን እየተማሩ ይገኛሉ።
አንድ ልጅ መሠረታዊ ማንነቱ የሚገነባው እስከ 10 ዓመት ባለው ዕድሜ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕፃናቱ በየመንደራቸው በቋንቋቸው አብረው መጫወትና መታረቅን ተምረው ማደጋቸው ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል።
በቅድመ መደበኛ ትምህርት ያለፉ ሕፃናት ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ ከዚህ ቀደም በስፋት ይስተዋል የነበረውን ከፍተኛ የትምህርት ማቋረጥ ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ዜጎች በሚሳተፉበት በዚህ የክረምት መርሐግብር፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው አቅመ ደካሞችን በማገዝና አካባቢያቸውን በማልማት ትልቅ ውለታ እየዋሉ ይገኛሉ። ይህ ተግባር ተማሪዎቹ ከማኅበረሰባቸው፣ ከባህላቸውና ከታሪካቸው ሳይነቀሉ መሠረታቸው ላይ የቆመ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ያግዛቸዋል።
ወጣቶች ይህንን የትብብር ተግባር እንደ ታላቅ የክብር ሥራ ሊወስዱት እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዛውንቶችም በበኩላቸው ለትውልዱ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ተረትን፣ ጸሎትን እና መሬትን ማክበርን እንዲያስተምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክተውም የሚከተለውን ጥልቅ መልእክት አስተላልፈዋል፦
"የማይሠራ እጅ በሚናገር አፍ ፍሬ አያፈራም። የሚሠራ እጅ፣ በሚናገር አፍና በሚያስብ አእምሮ ሲደገፍ ግን ብልጽግና ይረጋገጣል። አብዛኛው አሁን ያለንበት ችግር 'የማይሠሩ እጆች በሚናገሩ ብቻ አፎች' ተይዘው ልማትና ሰላም የሚመጣ መምሰሉ ነው።"
በመጨረሻም ከፊታችን ያለው ዘመን መሠረታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ችግሮች መልክ የሚይዙበት፣ ብዙ ድካምና ተጨባጭ ውጤት የሚጠበቅበት ወቅት በመሆኑ፤ መላው ዜጋ ክረምቱን፣ ዝናቡን እና ጊዜውን በመጠቀም በጋራ በመቆም ለኢትዮጵያ ብልጽግና የራሱን ጡብ እንዲያኖር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።