ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች በበጀት ሊሸፈኑ የማይችሉና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሊሶ ከተማ ተገኝተው የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብቻ 35 ሺህ የመዋለ ሕፃናት (ቅድመ መደበኛ) ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።
"ይህንን ሥራ መንግሥት አቅዶ ሊሠራው ቢነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መንግሥታት ተባብረው እንኳ ቢሞክሩት ለበርካታ ዓመታት የሚፈጅ ትልቅ ተግባር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
ይህም ሕፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ማኅበራዊ ትስስርን እንዲለምዱ፣ ባህላቸውን እንዲያውቁና ወደ አንደኛ ደረጃ ሲሸጋገሩም የትምህርት ማቋረጥ ሁኔታን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ አብራርተዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከትምህርት ቤቶች ግንባታ ባለፈ በርካታ ዘርፎችን ያቀፈ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስና መገንባት፣ የሀገር በቀል ዛፎችንና የፍራፍሬ ተክሎችን መትከል፣ የገጠር መንገዶችንና መለስተኛ ድልድዮችን በሕዝብ አቅም መገንባት እንዲሁም የጤና ኬላዎችንና ፋርማሲዎችን ማቋቋም ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና በመንግሥት በጀት ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ብልጽግና የሚረጋገጠው 130 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉልበቱን፣ ዕውቀቱንና ሀብቱን ሲደምር ነው" ብለዋል።
በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን የሚጠግ ሕዝብ የሚሳተፍበት ይህ ንቅናቄ፣ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ የሚመለሱ ወጣቶች ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀራረቡ፣ አረጋውያንን እንዲረዱና በተግባር የታገዘ ዕውቀት እንዲገበዩ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ "የሚሠራ እጅ፣ የሚናገር አፍና የሚያስብ አዕምሮ ሲሰናሰሉ ልማትና ለውጥ ይመጣል" በማለት፣ ወጣቶችና መላው ሕዝብ የክረምቱን ወቅትና ዝናቡን በመጠቀም ለሀገር ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘንድሮ በወሊሶ የተጀመረው ቤቶችን የመገንባትና የማደስ ሥራ በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ይህም የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይጠበቃል።