Search

7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ልዩ የሚያደርገው አካታችነቱ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ነው - ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 17

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካታች እና ስኬታማ ለማድረግ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ገልጸዋል።

ድምጽ ከተሰጠ በኋላም ቦርዱ ላለፉት 20 ቀናት በርካታ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ምክትል ሰብሳቢው አስታውቀዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ ቀደም ካሉት ልዩ የሚያደርገው ዋነኛው ስኬት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና አካታችነቱ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል።

ለዚህም እስከ ተፈናቃዮች ካምፕ፣ ወታደራዊ ሠፈሮች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በመሄድ ሰፊ የመራጮች ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ሰፊ የአየር ሰዓት ተደልድሎ 19 የፖሊሲ ክርክሮች በስኬት ተካሂደዋል።

ይህን ታሪካዊ ሂደት በነጻነት ለዓለም እንዲዘግቡም 1 ሺህ 827 የሀገር ውስጥ እና 45 የውጭ ጋዜጠኞች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ተገልጿል።

ምርጫው ከመጀመሩ በፊት በገለልተኛ ቡድን በተደረገ ግምገማ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ መኖሩን ቦርዱ አረጋግጦ ወደ ሥራ መግባቱ ተጠቁሟል።

በምርጫው ዕለት ያጋጠሙ እክሎችን ለመፍታት 663 አባላት ያሉት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የተሳተፈ ሲሆን፣ አቤቱታ በቀረበባቸው ክልሎችም በማጣራት ውሳኔ ተሰጥቷል።

ምርጫውን ሊያዛቡ በሞከሩ ሕገ-ወጥ አካላት ላይም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል።

በሂደቱ የዲጂታል ምዝገባ አጠቃቀም ችግሮች፣ የመረጃ ፍሰት ውስንነት፣ ረጃጅም ሰልፎች፣ የአንዳንድ አስፈጻሚዎች የብቃት እና የገለልተኝነት ክፍተት እንዲሁም የታችኛው መዋቅር አመራሮች ጣልቃ የመግባት ሙከራዎች በእጥረት ተነስተዋል።

ይሁንና ቦርዱ እነዚህን እክሎች በሕጋዊ መንገድ በመፍታት ስኬታማ ሥራ ማከናወኑን ምክትል ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድባቸው የተወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች ውጤት በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ ምክትል ሰብሳቢው አመላክተዋል።

በለሚ ታደሰ