Search

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ለምርጫው ስኬት ትልቅ ምሰሶ ነበር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 53

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ ባደረገበት መርሐ-ግብር ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ባደረጉት ንግግር፤ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ንቁ ተሳትፎ ለሂደቱ ሕጋዊነትና ስኬት ትልቅ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ ቦርዱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሁልጊዜ ግንኙነት በማድረግ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠትና ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊሲ ክርክር መድረኮችን በማዘጋጀት ምኅዳሩ በሀሳብ ፍልሚያ እንዲበለጽግ መደረጉን ጠቁመዋል።

ፓርቲዎቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በማንቀሳቀስ መራጩ ሕዝብ በትዕግስት ድምፅ እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

ምንም እንኳ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ቢያገኝም፣ የምርጫው ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት የጋራ ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቦርዱ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በሕግና መመሪያ መሰረት ብቻ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ በሀገር ውስጥ በለማ ቴክኖሎጂ የመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባ መከናወኑንና ጠንካራ የሎጂስቲክስ ስራ መሰራቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

May be an image of one or more people and dais

በምርጫው በታዛቢነት የተሳተፉት የአፍሪካ ኅብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖችም ከተፎካካሪ ኃይሎች እስከ መራጩ ሕዝብ የታየው ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በታዛቢነታቸው የምርጫ ጣቢያዎች አካታች መሆናቸውንና ሴቶች ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች መካከል ይበጀኛል ለሚሉት አካል ያለምንም ስጋት ድምፅ መስጠታቸውን መታዘባቸውን ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ በንግግራቸው አብራርተዋል።