የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር)ን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ውይይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ለምትጫወተው ወሳኝ ሚና ድርጅታቸው ያለውን አድናቆትና እውቅና ለመግለጽ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ስደተኞችን በብሔራዊ ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተትና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ብቻ ጥገኞች እንዳይሆኑ ለመርዳት በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የማካተት ፍኖተ ካርታን በአብነት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በፍኖተ ካርታው የትግበራ ሂደት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጋራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።