የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም (ኢቢሲ) ወደ ይዘት በሚል በጀመረው ጉዞ የተለያዩ መረጃዎችን በዲጂታል መንገድ እያደረሰ ይገኛል።
ኢቢሲ በውስጥ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ በትናትናው እለት በይፋ አስመርቆ ወደ አገልግሎት አስገብቷል።
አፕስቶር እና ፕሌይ ስቶር ላይ ተጭኖ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰዎች እየተዳረሰ ያለው መተግበሪያው፤ የኢቢሲን የቀጥታ ስርጭቶች እና የተለያዩ መሰናዶዎች ባሉበት ሆነው እንዲያገኙ እንደረዳቸው በርካቶች እየገለጹ ይገኛል።
ይህንን የሞባይል መተግበሪያ ያበለጸገው የኢቢሲ ዶት ስትሪም የኤአይ እና የአይሲቲ ዳይሬክተር የሆነው ዳግምልደት በቀለ፤ መተግበሪያው 6 የቴሌቪዥን እና 2 የራዲዮ የቀጥታ ስርጭቶችን ለ24 ሰዓታት መከታተል እንደሚያስችል አንስቷል፡፡
ኢቢሲ በራሱ አቅም ያበለጸገውን መተግበሪያ የጹሁፍ ዜናዎች፣ የምስል እና የድምጽ ዜናዎች በአንድ ቦታ ማቅረብ በማስቻሉ መተግበሪያውን በሀገራችን ልዩ ያደርገዋል ብሏል ባለሙያው።
ኢቢሲ ከቴሌቪዥን እና ከራዲዮ ስርጭቱ ባለፈ ለዲጂታላይዜሽን ቅድሚያ በመስጠት ከዘመኑ ጋር መዘመኑንም ገልጿል።
ዓለም ቅድሚያ ለዲጂታል እያለች በመሆኑ ኢቢሲም ይህንን እየተገበረ ስለመሆኑ ነው የገለጸው፡፡
መተግበሪያው በአነስተኛ የኢንተርኔት ዳታ ያለምንም መቆራረጥ ለአድማጭ ተመልካቾች መረጃዎችን ለማድረስ እንደሚያስችል ጠቁሞ፤ መተግበሪያው በእራሱ በቀጣይ ለተቋሙ የገቢ ምንጭነት እንደሚያገለግልም ነው ያስረዳው፡፡
መተግበሪያው ከቀጥታ ስርጭት በዘለለ ዩቲዩብ ላይ የተጫኑ ቪዲዮችንም ማግኘት እንደሚያስችልም ነው የተናገረው።
ኢቢሲ ከ20 በላይ የሚሆኑ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረጉን የገለጸው ዳግምልደት፤ ተቋሙ ዲጂታላይዜሽንን ዋና የሥራው አካል አድርጎ በተለያዩ ክፍሎች አየተገበረ ይገኛል ብሏል።
ሚዲያው ከሜይን ስትሪም ወደ ዲጂታል እየተሸጋገረ ያለበት ዘመን ላይ በመሆናችን፤ ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመሄድ ኢቢሲ በስፋት እየሰራ ይገኛል ሲልም አስረድቷል።
መተግበሪያውን በአጭር ጊዜ ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ያነሳው ባለሙያው፤ ከተጠቃሚዎች በሚገኘው ምላሽ መሰረት የሚሰሩ ተጨማሪ ማሻሻያዎች (አፕዴት) እነደሚኖርም ነው ያመላከተው።
ኢቢሲ የተለያዩ ሥራዎቹን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በማቀናጀት የጀመራቸውን ሥራዎች በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስቷል።
በተቋሙ የማኔጅመንት አባላት በሥራው ልዩ ድጋፍ እና እገዛ እንደተደረገለት የሚናገረው ዳግምልደት፤ ለዚህ ስኬት መድረስ ትልቅ ድጋፍ በመስጠታቸውም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
በሜሮን ንብረት
#EBC #ebcdotstream #Mobileapp #Digitalization