የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስኬት የተካሄደውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት ወንበሮችን ማሸነፋቸው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየሰፋ መመጣቱን በተግባር ያሳየ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ይህ ስኬት በክልል እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻለ የሀሳብ ብዝኃነት እንዲኖርና ጠንካራ የመንግሥት ተቋማትን የመገንባት ሂደትን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።
በተገለጸው የምርጫ ውጤት መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 438 መቀመጫዎችን ሲያገኝ፤ ኢዜማ 13፣ አብን 6፣ ነእፓ 3፣ መድረክ 3፣ አዴኃን 3፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 2 ወንበሮችን ያሸነፉ ሲሆን ሌሉች 10 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ የምክር ቤት ወንበር አግኝተዋል።
ለክልል ምክር ቤት በተደረገው ውድድርም ኢዜማ 73፣ ነእፓ 35፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት 34፣ ኦብነግ 20፣ ጉህዴን 14፣ መድረክ 11፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 6፣ ሕዳሴ ፓርቲ 5 እና ቤህነን 5 ወንበሮችን ማሸነፍ ችለዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ ምርጫው የሕዝብ ድምፅ መንግሥት ለመመስረት ብቸኛው መንገድ መሆኑንና መንግሥት የሚመሰረተው በኃይል ሳይሆን በሐሳብ ብቻ መሆኑን ያስተማረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አያይዘውም ፓርቲያቸው በሀገራዊ ጥቅም፣ በሉዓላዊነት፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ዙሪያ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ነጻነት ጣሰው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እስከ ታችኛው መዋቅር ተቀራርቦ መሥራት ሀገር ለማሻገር ቁልፍ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፣ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ፓርቲያቸው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በጥናት ለይቶ በማቅረብ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።