Search

ከገጠራማዋ መንደር እስከ ሕክምና ማማ፦ የኛንጋቶም ሕዝብ ያፈራው አዲሱ ሐኪም ዶ/ር ሶያ ኩሩፓ

እሑድ ሰኔ 21, 2018 83

በኛንጋቶም ወረዳ የታሪክ ማኅደር ውስጥ መቼም የማይረሳና በደማቅ ቀለም የሚጻፍ አዲስ ታሪክ ተሰርቷል።

ከአንዲት አነስተኛ ገጠራማ መንደር ተነስቶ፣ የሕይወትን ፈተናዎችና እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረዶችን ሁሉ በጽናት ያለፈው የአርብቶ አደሩ ልጅ ሶያ ኩሩፓ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርቱን በከፍተኛ ስኬት አጠናቆ የሕክምና ዶክተር (MD) በመሆን በይፋ ተመርቋል።

ዶ/ር ሶያ በወረዳው ታሪክ ውስጥ “የመጀመሪያው የኛንጋቶም ወረዳ ሕዝብ የሰው ልጅ ሐኪም” በመሆን ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ በክብር አስፍሯል።

ይህ ታላቅ ስኬት የዶ/ር ሶያ ጥረት ብቻ ሳይሆን የወረዳው አስተዳደርና የመላው የኛንጋቶም ሕዝብ የሰባት ዓመታት እልህ አስጨራሽ መስዋዕትነትና የፍቅር ውጤት ነው።

ወረዳውና ማኅበረሰቡ ለአፍታም ሳይሰለቹ፣ ምንም ዓይነት የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ ሳይነፍጉ፣ ለሰባት ዓመታት ሙሉ እንደ ዐይን ብሌናቸው እየተንከባከቡና አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ እየከፈሉ ያስተማሩት ልጃቸው፣ ዛሬ የሕዝቡን አደራ በድል ተወጥቶ ጋውን በመልበስ እውነተኛ የሕዝብ ወገን ሐኪም ለመሆን በቅቷል።

ይህ በደስታ አስለቃሽ የሆነ ድል ለሌሎች የአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ልጆች “እኛም መማርና ትልቅ ደረጃ መድረስ እንችላለን” የሚል ታላቅ ተስፋን የሰነቀ ሲሆን፣ የወረዳውን የጤና መዋቅር ይበልጥ ለማጠናከር አዲስ አቅምና ብርሃን የሚፈጥር ነው።

የኛንጋቶም ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ለዚህ ታሪካዊና ኩሩ ማዕረግ ለበቃው ለዶ/ር ሶያ፣ ለቤተሰቦቹ እንዲሁም ለሰባት ዓመታት ሙሉ ልጃቸውን ደግፈው ለዚህ ላበቁት ለኛንጋቶም ወረዳ ሕዝብና መንግሥት “እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት፣ ዶ/ር ሶያ ወደፊት በሚጠብቀው የሕዝብ አገልግሎት ላይ የላቀ ስኬትን ተመኝቷል።