የብሪክስ ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዙሪያ ያደረጉት ወሳኝ ውይይት እና የኢትዮጵያ ጥሪ
የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ልማት እንዲኖር በጋራ ለመስራት ጽኑ አቋም ያዙ።
ህንድ የ2026 የብሪክስ ፕሬዝዳንትነቷን ተከትሎ ባዘጋጀችው የመጀመሪያ የሳይንስ አካዳሚዎች ፎረም ላይ፣ ከአስር ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ስብሰባው ቴክኖሎጂው ለዘላቂ ልማትና ለዓለም አቀፍ ደቡብ (Global South) ሀገራት ትብብር እንዴት መዋል እንዳለበት በስፋት መክሯል።
በተለይም በበለጸጉት እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል እየሰፋ የመጣውን የቴክኖሎጂ አቅም አለመመጣጠን ለማጥበብ የሚያስችል የጋራ ማዕቀፍ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በዚህ መድረክ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት እና በዲጂታል ደህንነት ዙሪያ ጥልቅ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች።
በስብሰባው የቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቤላሩስ እና ግብፅ ተወካዮችም የየራሳቸውን ምክረ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሀገራቱ በጋራ የኮምፒውተር መሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት፣ በባለብዙ ቋንቋ የAI ሀብቶች እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ መጋራት ሥርዓት ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ከዚህ ስብሰባ የተገኙት ወሳኝ ግብዓቶች በሙሉ ተካተው፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ከጁላይ 22 እስከ 23 በሃይደራባድ በሚካሄደው ሁለተኛው የብሪክስ የሳይንስ አካዳሚዎች ስብሰባ ላይ የተሻሻለው መግለጫ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።