Search

ከቡና የወጪ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

ሓሙስ ሰኔ 25, 2018 67

ኢትዮጵያ በተገባደደው የ2018 በጀት ዓመት ከቡና ኤክስፖርት ለማግኘት አቅዳ የነበረውን 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማሳካት መቻሏን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

ሚኒስትሩ  እንደገለጹት፤ ባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ይህንን አሃዝ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል የተቻለው መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ነው።

በተለይም የቡና ምርትና ምርታማነትን በስፋት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውና ለምርት ጥራት ጥብቅ ክትትል መደረጉ ለተመዘገበው ታሪካዊ የዕቅድ ስኬት ከፍተኛውን ድርሻ ማበርከቱን አብራርተዋል።

አክለውም ይህንን ትልቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ስኬት ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን በመስራት የበኩላቸውን የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የቡናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በሙሉ በግብርና ሚኒስቴር ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።