Search

የኢትዮጵያን የጥብቅ ተፈጥሮ ሀብቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመጠበቅ የሚያስችለው 'አትላስ' የድረገፅ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

ሓሙስ ሰኔ 25, 2018 74

በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመከታተል፣ ለመጠበቅ እና ለመቆጣጠር የሚያስችል “አትላስ”የተሰኘ አዲስ የድረገፅ መተግበሪያ ዛሬ በይፋ ተመርቋል፡፡

በሚቀጥሉት ሳምንታት ስራ የሚጀምረው መተግበሪያው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ ያበለጸጉት ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በተለይ ለባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ለሰንቀሌ የቆርኪዎች መጠለያ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ተዘጋጅቷል።

በሁለቱ ተቋማት ቅንጅት የተገኘው ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበትና የዱር እንስሳት መረጃ በዲጂታል መንገድ በማደራጀት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለማስገኘት ያለመ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፤ ዘመናዊ የዲጂታል ካርታዎችንና የጥብቅ ቦታ መረጃዎችን ለጎብኚዎች ማቅረብ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል። ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጂራ በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያለውን ውስን የሰው ኃይል በዘመናዊ መሣሪያ በመደገፍ ውጤታማ የመስክ ስምሪትና ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር)፤ ይህ የዲጂታል ሽግግር ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለምርምር ተቋማትና ለዓለም አቀፍ አጋሮች ከግምትና ከአድሎ የጸዳ፣ በማስረጃ ላይ የተደገፈ ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ ለማድረስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ወጣቶች በመተግበሪያው አማካኝነት እንደ ደን መጨፍጨፍ፣ የሰደድ እሳት ወይም በዱር እንስሳት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በቀጥታ ለቁጥጥር ማዕከል ሪፖርት የሚያደርጉበት ሥርዓት ይዘረጋል። ይህም ህዝባዊ ተሳትፎንና የባለቤትነት ስሜትን እንደሚያጎለብት ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ106 በላይ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ይህ መተግበሪያ ለእነዚህ ሀብቶች መጠበቅ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።

በወይነሸት ደጀኔ