የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር መድረክ አሉ የሚባሉ አጀንዳዎች ሁሉ ቀርበው" ከሰማይ በታች" ሊባል በሚችል ደረጃ ማናቸውንም ሀገራዊ ጉዳዮች ለማስተናገድ ሰፊውን ማዕድ አዘጋጅቶ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
የምክክሩ ሂደት ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን ለመፍታት በሃሳብ ላይ የተመሰረተ ልውውጥን ብቻ መሰረት በማድረግ ጠንካራ ሀገረመንግስት ለመገንባት የተወሰደ ታላቅ የትውልድ እርምጃ ነው፡፡
ይህ መድረክ ሂደቱ በታሪክ ታይቶ የማያውቀውን ስለሀገራችን ተመካክረን እንወስን የሚል ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ አግኝተው የማያውቁትን የመጀመርያና ታሪካዊ ዕድል የከፈተ መድረክ ነው፡፡ መድረኩ ሂደቱ ገለልተኛና አሳታፊ ሁሉን አካታች ከመሆኑ ውጪ ውጤቱ ግን ማንኛውም ሀይል ቀድሞ ሊያውቀው የሚችል አይደለም፡፡
ለዘመናት አንተ ሳትሆን ስለሀገር እኔ አውቅልሀለው በሚል ፈሊጥ እድል ያገኘና ጠመንጃ ያነገበ ሁሉ እኔ ያልኩት ቃል የመጨረሻው እውነት ነው፣ እኔ ያልኩት ነው ትክክል እያለ በሌላው ጫንቃ ላይ በጉልበት ሲጭን ፣ሌላውን ሲያስገብር የኖረ በመሆኑ ተመካክሮ ተደራድሮ የጋራ አቋም ወስዶ አንዳንዴም ለብዙሃን ሲል የራሱን አቋም ቀይሮ አሻሽሎ መኖርን እንደ ሽንፈትና ክሽፈት ስለሚመለከት ምክክርን አጥብቆ ይፈራል፡፡
ምክክር ውጤቱ የሂደቱ ምርት ነው፡፡ ቀድሞ የታወቀ ነገር ምክክር አያስፈልገውም፡፡ እኛ የምንፈልገው ወይም የማንፈልገው ነገር በውጤቱ ከመጣ ምክክሩ ከሽፏል ልንል አንችልም፡፡ እናም የምክክር ውጤት ለብዙሃን የመገዛትን ለሃሳብ የበላይነት መንበርከክን የሚያመጣ በመሆኑ የእኔ አውቅልሀለው ፖለቲከኞች በጭራሽ ሊቀበሉት አይችሉም፡፡
ይልቁንም ለምክክሩ ጭራና ቀንድ እያበቀሉለት ሂደቱን ለማደናቀፍና ያለ ውጤት እንዲቀር ያለማሰላሰል መስራታቸው አይቀርም፡፡ መንግስት ይህ ምክክር እውን እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰርቷል ፣ደክሟል። መንግስት እንደባለፉት ስርዓታት በእኔ አውቅልሀለው መርህ የሚፈልገውን ስርዓት አስፍኖ ጊዜው እስከፈቀደለት ድረስ መግዛት የሚከብደው ባልሆነ ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ነውና፡፡ ነገር ግን ያለፉት ስርዓታት በዚህ መንገድ ብሄራዊ መግባባትም ሆነ የጠንካራ ሀገረመንግስት መገንባት አልቻሉም፡፡
ማንም የዛሬዋና የነገዋ ኢትዮጵያ ላይ የግል ፍላጎቱንና ምኞቱን ጭኖ ፀንቶ መቆየት ፈፅሞ አይቻለውም፡፡ ስለዚህ ይህ ትውልድ ኢትዮጵያን በሰለጠነ መንገድ መክረው የነገዋን መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ይችላሉ ብሎ ቆርጦ ተነስቷል፡፡
ምክክሩ የትኛውንም ሀይል ያገለለ አይደለም፣ አልነበረምም፡፡ ለሁሉም ሀይሎች እስከ ጥግ ድረስ ሄዶ ለማሳተፍ የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡
ሆኖም ግን ይህ መድረክ የፈውስ መድረክ እውን እንዳይሆን የሚመኙና የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ተኮላሽቶ እንዲቀር ሌት ተቀን የሚሰሩ ኃይሎች፣ ገና ሳይጀመር ሂደቱን ለማጠልሸት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ የተለመዱ ጥርጣሬ ይፈጥርልናል በሚሉት ጉዳዮች የተዛቡ ትርክቶችን ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡
ይህም ሀገራችን ከጀመረችው ታሪካዊ የሃሳብ ግንባታ መድረክ በማውጣት ወደ ቀደመው የመጠፋፋት ቁማር ለመመለስና ህዝብ በሂደቱ ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ ታቅደው የሚሰራጩ አፍራሽ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ነው። እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ችግሮቿን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትታ፣ ጽንፈኛ ትርክቶቿን አክማ ጸንታ እንድትቆም የማይፈልጉና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞች የማሳጣት የቆየ አጀንዳ ያነገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ያውቀዋል።
እውነታው ግን ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የልብ ትርታ የሚያዳምጥ የጋራ የሀሳብ አውድማ ነው። የትኛውም ኢትዮጵያዊ፣ አልፎ ተርፎም መንግሥትን በጦር መሳሪያ እየተዋጉ ያሉ ኃይሎች ጭምር፣ አጀንዳቸውን ይዘው የመቅረብ ሙሉ መብትና ሰፊ ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።
አጀንዳ ይዞ መቅረብ ማለት ውሳኔን ማጽደቅ ሳይሆን፣ በሀሳብ ገበያ ላይ ዴሞክራሲያዊ አማራጭን ይዞ መሞገት ማለት ነው።
የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ምክክር ፋይዳ፣ ላለፉት ዘመናት የተሰነጣጠቅንባቸውን የፖለቲካ ስብራቶች አክሞ፣ ኢትዮጵያን በስምምነትና በትብብር ዴሞክራሲ (Consociational Democracy) ሞዴል ላይ ማጽናት ነው። ይህ የትብብር ዴሞክራሲ፣ ሀገራችን ችግሮቿን በመነጋገር እያረቀች፣ በሃሳብ ልዕልና እየተገነባች የምትሄድ፣ የሁሉንም ድምፅ የምታስተናግድ ጠንካራ ሀገር እንድትሆን ብቸኛው መፍትሔ ነው።
መንግሥት ይህንን የፈውስ መድረክ አምኖበት በማምጣትና ከፍተኛ ርቀት በመጓዝ ለስኬቱ ያለውን የማያወላውል ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል። በመሆኑም፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህን አፍራሽ ኃይሎች ተንኮል ነቅቶ በመረዳት፣ የተጀመረውን የውይይትና የጋራ መግባባት ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ሊደግፈውና ሊያበረታታው ይገባል። ኢትዮጵያ የምትድነውና የምትሻገረው፣ አንዳችን ሌላውን በማጥፋት ሳይሆን፣ የጋራ እምነት በምንይዝባቸው ጉዳዮች ላይ በጽኑ ተባብረን ስንሰራ ብቻ ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ