የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ (KPLC) ጋር አዲስ የኃይል አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በ24 ብር ከ07 ሳንቲም፣ እንዲሁም ለዲማንድ ቻርጅ 1 ሺህ 10 ብር ከ89 ሳንቲም ታሳቢ በማድረግ ለጎረቤት ሀገር ኬንያ የምታቀርብ ይሆናል።
ይህንን ስትራቴጂካዊ ስምምነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እና የኬንያው አቻቸው ኢንጂነር ጆሴፍ ሲሮር (ዶ/ር) በጋራ ፈርመውታል።
ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የኤሌክትሪክ ንግድ ከማሳደግ ባለፈ፣ በድንበር አካባቢ ለሚገኙ ማህበረሰቦች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን በማስፋፋት የምስራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ኢንጂነር ጌቱ እንደገለጹት፣ ኢነርጂ የሀብት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የሚያሸጋግር ጠንካራ ድልድይ ነው።
የኬንያው አቻቸው ጆሴፍ በበኩላቸው፣ ይህ የኃይል ትስስር ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ባሻገር በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን ሰላምና የኢኮኖሚ ትብብር በእጅጉ እንደሚያጠናክረው አብራርተዋል።
ይህ እርምጃ በሀገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ከማሻሻል አልፎ፣ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተቀናጀ የኃይል አቅርቦት ስርዓት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: