እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) አደረሳችሁ!
መውሊድ ታላላቆቻችንን የምናስብበት፣ መተባበርና አብሮነት፣ መተዛዘንና መፈቃቀድ በተግባር የሚገለጽበት ነው። ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ ማኅበራዊ ትሥሥር የሚጠናከርበትና በአንድነት አብሮ የሚያሳልፉት ታላቅ በዓል ነው።
ይህን በዓል የምናከብረው የዓለሙ እዝነት፣ ለሠናዮች መልካሙን አብሣሪ፣ ለተከታዮቻቸው ሐላል እና ሐራሙን አስተማሪ የሆኑት ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮና መልካም ሥራ የሚታወስበት፣ የሚዘከሩበትና የሚወደሱበት በመሆኑ ነው።
የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ተግባራት ሳይደበዝዙ በድምቀት፣ ሳይሻሩ በህያውነት ዛሬም ድረስ አሉ። ይህን በዓል በጋራ ስናከብር በተሟላ የመልካምነት ዕሴት፣ በፍቅር እና በአብሮነት፣ በሰላም፣ በመተሳሰብ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት ሊሆን ይገባል።
ለቆምንለት በጎ ዓላማ መትጋትን፣ ለሌሎች የሚተርፍ መልካም ፍሬ መስጠትን፣ ሀገርና ሕዝብ የሚያወሱት ዐሻራን ማሳረፍ፣ በኅብረት መሥራት፣ በጽናት መቆምና በዕውቀትና በትዕግሥት ወደ ግባችን መገሥገሥም ያስፈልጋል።
በድጋሜ እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: