የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1 ሺህ 5መቶ አንደኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት (መውሊድ) መታሰቢያ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን በአክብሮት ገልጿል።
ጉባኤው ባስተላለፈው መልዕክት፣ የዘንድሮው የመውሊድ በዓል የሚከበረው ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሀገራዊ ምክክር በስኬት በተጠናቀቀበት ማግስት በመሆኑ የበዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ እንደሚያደርገው አመልክቷል።
ሂደቱ የሀሳብና የፍላጎት ልዩነቶች የታዩበት ቢሆንም፣ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በመግባባት የተጠናቀቀ ታሪካዊ ስኬት መሆኑንና ለዚህም የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጾ፣ በቀጣይም ስምምነቶቹን በተግባር ለመተርጎም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቱ የጸና መሆኑን አስታውቋል።
የዘንድሮው በዓል "የፍትሑ ነብይ" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የጠቀሰው ጉባኤው፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኖሩበት ዘመን ለሰው ዘር ሁሉ ሰብአዊነትን፣ ፍቅርን፣ አክብሮትንና ርህራሄን በማሳየት በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረውን በደልና ኢሰብአዊነት ለማረም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አብራርቷል።
በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ለፍትህ የከፈሉትን ዋጋ በማሰብ እና ፍትህ በምድራችን በሙላት ይሰፍን ዘንድ ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።
በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር በሕመም አልጋ ላይ፣ በሕግ ጥላ ስር እና በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማበረታታትና ያለንን በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ ያቀረበው ጉባኤው፣ ለአገራችን ሰላም፣ ለሕዝባችን አንድነትና በረከት ዱዓ በማድረግ እንዲሆን በመጠየቅ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ መልካም የበዓል ምኞቱን አስተላልፏል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: