Search

በምክክር ጉባኤው እንደ ሀገር ሥር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮች ዙሪያ የጋራ መግባባት እንደሚፈጠር እንጠብቃለን - የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

ቅዳሜ ሐምሌ 04, 2018 136

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታካሂደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እንደ ሀገር ያደሩ እና ለዘመናት የተከማቹ ልዩነቶችን ከማጥበብ ባለፈ አብሮነትን በመገንባት ረገድ አይተኬ ሚና እንዳለው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ምክክር የተለያዩ የተቃርኖ ሐሳቦችን የምናርቅበት፣ ነጣጣይ እና የተሳሳቱ ትርክቶችን የምናርምበት፣ ብሔራዊ አንድነታችንን እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን የምናስከብርበት የችግሮቻችን ሁሉ ቁልፍ መሣሪያ ስለመሆኑ ነው የገለጹት።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ አስታራቂ እምነቶች፣ የባህል እሴቶች ባለቤት ብትሆንም እርስ በርስ የመነጋገር እና የመወያየት ባህላችን ደካማ በመሆኑ ለብዙ ተግዳሮቶች ስንጋለጥ ቆይተናል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ አሁን ላይ ግን እንደ ሀገር በታሪክ አጋጣሚ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥያቄዎቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ከሐምሌ 8 ጀምሮ የሚካሄደውን የምክክር ጉባኤን በጉጉት እና በተስፋ እንደሚጠብቁትም ተናግረዋል።

በክልሉ በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍም የተለያዩ አጀንዳዎችን ለምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ከቀናት በኋላ በሚጀምረው ጉባኤ እንደ ሀገር ሥር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮችን ጨምሮ ያነሧቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች እንደሚመለሱላቸው በተስፋ እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል።

ሀገር የምትገነባው በንግግር እና በምክክር በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም፣ ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ እና ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መከበር በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለጉባኤው ስኬትም መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን በቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተስፋሁን ደስታ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: