Search

ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበሪያ ስልታዊ ጋሻ ነው

ቅዳሜ ሐምሌ 04, 2018 153

አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረክ የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖረው፣ ብሔራዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር እና ሉዓላዊነቱን ለማስጠበቅ ቀዳሚው እና ወሳኙ መስፈርት ጠንካራ የውስጥ አንድነት መገንባት ነው።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር የውስጥ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ረገድ የሚኖረው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሀገርን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር አንፃር የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግል ታላቅ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ዋነኛው ጠቀሜታ በዋና ዋና የሀገር ህልውና እና ጥቅሞች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠሩ ላይ ነው።

እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የባሕር በር ፍላጎት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ባሉ ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሁሉም ዜጋ እና የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ወጥ አቋም እንዲኖር ያደርጋል።

ይህ በምክክሩ የሚመጣው የጋራ አቋም የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ልዩነት መሃል እየገቡ የሀገርን ጥቅም ለመጋፋት እና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ለመፍጠር የሚያደርጉትን ማንኛውንም ድብቅ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚዘጋ ነው።

ታሪክ እና የጂኦፖለቲካ ሳይንስ እንደሚያረጋግጠው የውስጥ መከፋፈል ያለበት ሀገር ከውጭ የሚመጣበትን ጥቅምን የማስከበር ግፊት በብቃት መመከት አይችልም።

ስለዚህም በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ለውስጣዊ ስምምነት ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን የተደማጭነት እና የተጠቃሚነት አቅም ከፍ የሚያደርግ ነው።

ይህ ሂደት በተባበረ ክንድ እና በአንድ ብሔራዊ ራዕይ የምትመራ ጠንካራ ሀገርን በመገንባት ክብር እና ብሔራዊ ጥቅሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: