የአየር ንብረት መዛባት መላውን ዓለም በፈተና ላይ በጣለበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ከተለመደው የተቃውሞ እና የጭንቀት ጩኸት ባለፈ በተግባር የሚታይ ታላቅ ምላሽ እየሰጠች ትገኛለች።
ዘንድሮም “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው ሀገራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ከችግኝ ተከላነቱ ባለፈ የነገዋን አረንጓዴ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ትልቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህም ባለፉት 7 ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል የቻለችው ሀገራችን በያዝነው ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ተግባር ገብታለች።
ይህ መርሐ ግብር ተራራዎቻችንን ችግኝ ከማልበስ ባለፈ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለትውልድ የሚተርፍ የተስፋ ስንቅ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመላው ሀገራችን ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት እና ብዙ ሚሊዮን ዜጎች በነቂስ ወጥተው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ጉዞ የራሱን ዐሻራ ያሳረፈበት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚዘጋጁ ችግኞች እንደ ከዚህ ቀደሙ ለደን ልማት ብቻ ሳይሆን፣ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ፍራፍሬ፣ ቡና እና የቅመም እፅዋት ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
በዚህም መሰረት መርሐ ግብሩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ መርሐ ግብርም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ዘንድሮም ከሕፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግሥት ሠራተኞች እስከ ግል ባለሀብቶች፣ ተማሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች በጋራ በመውጣት “ተስፋን የመትከል” ድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም 17.2 ከነበረበት አሁን ላይ ወደ 23.6 በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡
ይህም ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከፍ አድርጎታል።
ችግኝ መትከል የመጀመርያው ምዕራፍ እንጂ የመጨረሻ ባለመሆኑ የተከልነውን ተስፋ አጽድቀን ለውጤት ማብቃት ይጠበቅብናል።
በዚህ ረገድም በመርሐ ግብሩ ችግኝን መንከባከብ ከመትከል እኩል ትኩረት ተሰጥቶት ስለተሠራበት የጽድቀት መጠኑ ከ85 በመቶ በላይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ዛሬ የምንተክለው አረንጓዴ ዐሻራ ነገ ለልጆቻችን የሚጠለሉበት ጥላ፣ የሚተነፍሱት ንጹህ አየር እና የሚመገቡት ፍሬ ይሆናል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: