የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚያካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሚሳተፉ ተመካካሪዎች የቅድመ ምክክር ገለጻ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየሰጠ ነው።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሀገራቸው ሰላም፣ ሀገር ግንባታ፣ ሰብዓዊ መብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገርና ለመደማመጥ በአንድነት መሰባሰባቸው ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ትናንት ሀገር ሲመሰረትና ነፃነቷ ሲጠበቅ በአንድነትና በኅብረት ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ በረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ የተፈጠሩ አለመግባባቶችንና ቁርሾዎችን ለመፍታት መነጋገራችን፤ ከችግሮቻችን ለመውጣት ያለንን ፅኑ እምነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ምክክሩ በሚመራበት ስልት እና ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ሚና ላይ ሰፊ ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል።
በዚህም አጠቃላይ የምክክር ሂደቶች፣ የቡድን አደረጃጀት እና መዋቅር፣ የምክክሩ መመሪያ እሴቶች አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ትብብር፣ እኩልነት፣ መልካም ግንኙነት ግንባታ፣ የመላው ቡድን አስተሳሰብን ማሳደግ እና ሙሉ ስምምነት ፍለጋ መሆናቸው ተመላክቷል።
እንዲሁም ዝርዝር የምክክር ሂደቶች፣ የጊዜ ሰሌዳ እና ማጠቃለያ ሐሳቦችን በሚመለከት ተሳትፎው እንዴት መሆን አለበት የሚለው ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ይህ መድረክ ተሳታፊዎች በምክክሩ ላይ በምን መልኩ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደ ጋራ መግባባት ለመድረስ የሚደረገውን ጉዞ በይፋ የከፈተና ቀጣይነት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
በነፃነት ፍቅሩ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: