Search

ቀይ ባሕረኞች ነን!!

ቅዳሜ ሐምሌ 04, 2018 162

ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር በታሪክ፣ በደም፣ በሃይማኖት እና በጂኦፖለቲካዊ ትሥሥር የተገመዱ፣ ፈፅሞ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ አካል ሁለት ገጽታዎች ናቸው።

እኛ የቀይ ባሕር ሕዝቦች ነን፤ ቀይ ባሕረኞችም ነን። ታሪካችን፣ ሥልጣኔያችን እና የዘመናት የታላቅነታችን ምስጢር የተቀበረው በዚሁ ስትራቴጂያዊ የውኃ አካል እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ሞገዶች ውስጥ ነው።

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያውያን መልክዓ ምድራዊ የውኃ አካል ብቻ ሳይሆን፣ የሕልውና፣ የክብር፣ የነጻነት እና የደኅንነት ጉዳይ ነው።

በቅዱሳት መጻሕፍት ሳይቀር ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ ጋር በጥብቅ አስተሣሥሮ በበርካታ ስፍራዎች እናገኘዋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላላቅ ተዓምራት የተፈጸሙበት ይህ ባሕር (በጥንት ስሙ "ባሕረ ኤርትራ" ወይም በዕብራይስጥ "ያም ሱፍ" እየተባለ የሚጠራው) ከጥንታውያን የኢትዮጵያ አባቶች መንፈሳዊ እና ንግዳዊ ታሪክ ጋር የተሣሠረ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ እና ከፅርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ወደ ግዕዝ ሲተረጉሙ፣ ይህ የውኃ አካል የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ መድረክ መሆኑን አብረው አስፍረዋል።

በተጨማሪም፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከመካ መከራ ፍትሕ ወዳለባት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ (አል-ሐበሻ) ሲሰደዱ በሰላም የተሻገሩት ይህንኑ ቀይ ባሕር ነው። በመሆኑም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያውያን የመከራ ጊዜ መሸሸጊያ፣ የፍትሕ በር እና የእምነት ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።

በታሪክ ድርሳናት እንደሰፈረው፣ እኛ ለቀይ ባሕር ደኅንነት ስንፋለም የኖርን ሕዝቦች ነን። በዘመነ አክሱም፣ ኢትዮጵያ ከሮም፣ ፋርስ እና ቻይና ጋር ተወዳድራ ከዓለም አራት ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት አንዷ ለመሆን የቻለችው ቀይ ባሕርን በማስተዳደር እና በመቆጣጠር ነበር።

የአክሱም ነገሥታት ስትራቴጂያዊ የሆነውን የአዱሊስ ወደብን በመቆጣጠር፣ ከሜዲትራኒያን ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ያለውን ረጅም የንግድ መስመር ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ሲጠብቁ እና የዓለምን የንግድ ፍሰት ሰላም ሲያስከብሩ ኖረዋል። አጼ ካሌብ በቀይ ባሕር አቋርጠው በመዝመት በየመን (ሂምያር) በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ በማስቆም የቀይ ባሕርን ሰላም እና ደኅንነት በኃይል አስከብረዋል።

ይህ የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያውያን የቀይ ባሕር ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የባሕሩ ታማኝ ዘብ፣ ፈር ቀዳጅ እና የደኅንነቱ አስተማማኝ ዋስትና ጭምር እንደነበሩ ነው።

ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ዕጣ ፈንታ ፈጽሞ የተቆራኘ ነው። ቀይ ባሕር የዓለም አቀፍ ታላላቅ ኃያላን የጦርነት፣ የውክልና እና የኢኮኖሚ ፉክክር አውድማ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ የቀጣናው ሰላም እና የባሕሩ ደኅንነት አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያን የመሰለ ታሪካዊ ባለቤት እና ጠንካራ ሀገር የባሕር ላይ ደኅንነት ዋነኛ አካል ስትሆን ብቻ ነው።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር መገለሏ፣ የተፈጥሮን ሕግም ሆነ የታሪክን ፍሰት የሚቃረን ፖለቲካዊ ክስተት ነው።

በአጠቃላይ፣ እኛ ቀይ ባሕረኞች ነን። የኢትዮጵያ የዘመናት የታላቅነት ምስጢር፣ እንዲሁም የወደፊቱ እምቅ አቅም ያለው እዚያው የባሕሩ ዳርቻ ላይ ነው። በታሪክ፣ በባሕል እና በጂኦግራፊያዊ መስተጋብር ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር የልብ ትርታ ናት።

ቀይ ባሕር ያለ ኢትዮጵያ ደኅንነት እና ጥበቃ፣ ኢትዮጵያም ያለ ቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካዊ ሙሉነት አይኖራቸውም። የነገው የኢትዮጵያ ብልጽግና እና የቀጣናው ዘላቂ ሰላም እውን የሚሆነው፣ ይህ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትሥሥር ዳግም ሕያው ሲሆን እና ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ደም ገብረው ወዳቆዩት ተፈጥሯዊ የባሕር በራቸው በልማት ዲፕሎማሲ እና በጋራ ተጠቃሚነት አዲስ የትሥሥር መንፈስ ሲመለሱ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: