Search

ከፓሽቱን ‘ጂርጋ’ የሚልቀው እሴታችን

ቅዳሜ ሐምሌ 04, 2018 135

በፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ድንበር ተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩት የፓሽቱን ጎሳዎች፣ ለዘመናት "ባዳል" (Badal) በሚሉት እጅግ አስፈሪ የደም መፋሰስ እና የበቀል ባህል ውስጥ ሲኖሩ የቆዩ ናቸው።

በአንድ ቀላል ግጭት የሚነሳ ጠብ፣ በቀሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ፣ ማሳዎችን ሲያወድም፣ አባዎራዎችን ሲያጠፋ እና መንደሮችን ሲያፈርስ ኖሯል። ይህ ማለቂያ የሌለው የጥላቻ እና የቂም ሸለቆ፣ ዘላቂ መፍትሄ ያገኘው "ጂርጋ" በሚባለው ጥንታዊ እና ታላቅ የሽማግሌዎች የጋራ የምክክር ሸንጎ  ነው።

ግጭቱ እጅግ ሲያማርራቸው እና የሕዝቡን ኅልውና ሲፈታተን፣ የተለያየ ጎራ የያዙ የጎሳ መሪዎች፣ አዛውንቶች እና ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያቸውን ከሸንጎው ውጪ ጥለው ተሰበሰቡ።

በጂርጋው ሥርዓት ሁሉም ተሳታፊ በክብ ቅርጽ መሬት ላይ አብሮ ተቀመጠ፤ በዚህም የበላይ እና የበታች፣ የፊት እና የኋላ ወይም የክብር ቦታ የሚባል አልነበረም። ሁሉም እኩል ነው።

እያንዳንዱ ሰው ሐሳቡን፣ ቁስሉን እና ብሶቱን የመናገር እንዲሁም የመከራከር ሙሉ መብት ተሰጠው። ማንም ሰው የሌላውን ንግግር አያቋርጥም። መፍትሄውም አሸናፊ እና ተሸናፊ በሚፈጥር የድምጽ ብልጫ ሳይሆን፣ ሁሉም በሚያምንበት የጋራ መግባባት እና ስምምነት (Consensus) ላይ ብቻ ተመሰረተ።

ለዘመናት ደም ሲቃቡ የነበሩ፣ መተያየት የማይችሉ ጎሳዎች፣ በዚህ ጥልቅ የምክክር ሸንጎ አማካኝነት ይቅር ተባብለው፣ ተቃቅፈው፣ የጥላቻውን ገደል ዘግተው ወደ ሰላም ተመለሱ።

ሐቁን እንነጋገር ከተባለ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፓሽቱን ጂርጋም በላቀ እና እጅግ ጥልቅ በሆነ መልኩ ለዘመናት የዳበረ የመመካከር፣ የይቅርታ እና የመደማመጥ ማህበራዊ እሴት ያላት የጥበብ ማህጸን ናት።

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የዳበረው እና ዓለም ያደነቀው ገዳ ሥርዓትከኦዳ ዛፍ ስር ቁጭ ብሎ የሕዝብን ብሶት በነጻነት የማዳመጥ፣ በመከባበር የመከራከር እና ፍትህ የማንገስ እጅግ የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ አውድማ ነው።

በጉራጌው ማኅበረሰብ ዘንድ በታላቅ ክብር የሚታወቀው ጆካባህላዊ የምክክር ሸንጎ፣ በአፋሩማዳዓ በሲዳማውሶንጎእንዲሁም በሁሉም የሀገራችን ጥግ የሚገኘው ሀገር ሽማግሌሥርዓት፣ ኢትዮጵያውያን ክፉ የተባለውን የልዩነት ሸለቆ በንግግር እና በጋራ ምክክር የመድፈን ታላቅ ሀገር በቀል ማኅበራዊ ካፒታል ያላቸው ሕዝቦች መሆናችንን በግልጽ ይመሰክራል።

እኛ ኢትዮጵያውያን መደማመጥ በባህላችን፣ መቻቻል በእሴታችን፣ መከባበር በደማችን ውስጥ አለ። በባህላዊ ሸንጎዎቻችን አንድ ሰው ሐሳቡን ሲገልጽ አይቋረጥም፤ ትንሹም ትልቁም እኩል የመደመጥ መብት አለው።

መፍትሄውም በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ በሚፈጥር አግላይ መንገድ አይደለም። ይህ ድንቅ ሀገር በቀል እሴታችን ነው በታሪክ አጋጣሚ ሁሉ ሀገራችንን ጠብቆ ያቆያት።

አሁን ደግሞ የፊታችን ሐምሌ 8 ቀን ለሚጀመረው ታላቁ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እነዚህን ህያው ባህላዊ እሴቶቻችንን ከመደርደሪያ አውርደን ወደ መድረኩ መሀል ልናመጣቸው ይገባል።

ዘመናዊ የፖለቲካ ጽንሰ-ሐሳቦችን ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ሀገር በቀል የመደማመጥ፣ የመቻቻል እና የሰከነ የውይይት ጥበባችንን መሳሪያ አድርገን መጠቀም አለብን።

ወደ ጠረጴዛው ስንመጣ የፖለቲካ እልህን፣ የትርክት ግትርነትን እና ስሜታዊነትን ከልባችን ስር ነቅለን በመጣል፤ የገዳን የማዳመጥ ትዕግስት፣ የጆካን ሚዛናዊነት እና የሽማግሌን እርጋታ ተላብሰን የሰከነ ውይይት ለማድረግ መዘጋጀት ይኖርብናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የውጭ ተጽዕኖን ወደ ጎን ትተን፣ አባቶቻችን ባስተማሩን የጠረጴዛ ዙሪያ እና የዋርካ ስር የውይይት ስልት ከተነጋገርን፣ የማይፈታ ችግር ፈጽሞ አይኖርም።

የጋራ ሸንጓችንን እና ሀገር በቀል እሴታችንን ከዘመናዊ አሠራር ጋር ካዋሄድነው፤ ልዩነቶቻችን የቱንም ያህል ቢሰፉ በመመካከር እና በሰከነ ውይይት የማይደፈን የልዩነት ሸለቆ በኢትዮጵያችን ምድር ፈጽሞ ሊኖር አይችልም።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: