የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘንድሮው በጀት ዓመት የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5 በመቶ እንዲሆን ወስኗል፡፡
ይህንን ሕግ በሚተላለፉ አከራዮች ላይ ከባድ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣል ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል።
ኃላፊዋ እንደገለጹት ይህ የጭማሪ ጣሪያ የተወሰነው የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ፣ የተከራዮችን የመክፈል አቅም፣ የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶበት ነው።
ጥናቱ በገለልተኝነት እና በሳይንሳዊ መንገድ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎ የተደረገ በመሆኑ አከራዮች ከዚህ ጣሪያ በላይ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ ኃላፊዋ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ አከራዮች ከዚህ ጣሪያ በታች በሆነ ዋጋ ማከራየት ወይም ጭራሽ ያለመጨመር ሙሉ መብት እንዳላቸው የገለጹት ወ/ሮ ቅድስት፤ አሠራሩ አከራዮች በተከራዮቻቸው ላይ የዘፈቀደ ጭማሪ እንዳያደርጉ የሚገድብ በመሆኑ ለተከራዮች ትልቅ የደኅንነት እና የመረጋጋት ስሜት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ቤት ቋሚ ንብረት በመሆኑ በየዓመቱ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ ግዴታ አለመሆኑን ያነሱት ኃላፊዋ፣ 11.5 በመቶ ጭማሪው ለተከራዩም አቅም የሚመጥን እንዲሁም ለአከራዩም ቤቱን ለማደስ እና ለመጠገን የሚያስችል በቂ ምጣኔ ነው ብለዋል።
ሕጉን በመተላለፍ ከ11.5 በመቶ በላይ የኪራይ ጭማሪ በሚጠይቁ፣ ውል ሳያድሱ ወይም ሳይመዘግቡ በሚገኙ አከራዮች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት የኪራይ ውል ጊዜያቸው ካበቃ በኋላ ውላቸውን ሳያድሱ ለተወሰኑ ወራት የሚቆዩ አከራይ እና ተከራዮች እንደየሁኔታው ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር የቤት ኪራይ መጠን ቅጣት ይጣልባቸዋል።
በተጨማሪም በሰፈር ወይም በቃል ስምምነት ብቻ በማከራየት የተገኙ አካላትም እንደ ጥሰቱ ክብደት ከአንድ እስከ ሦስት ወር የቤት ኪራይ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ይህንን አሠራር ተግባራዊ ያደረገው በተከራዮች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመከላከል እና በአከራይ እና ተከራይ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
አከራዮች ይህንን የዋጋ ጣሪያ እንደ መብት ሳይሆን መከበር ያለበት ሕጋዊ ገደብ አድርገው ሊመለከቱት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ማንኛውም ተከራይ አከራዩ ከዚህ ጣሪያ በላይ በመጠየቅ የሚያንገላታው ከሆነ ወይም ሕገ-ወጥ የውል ስምምነት ከተጠየቀ በነጻ የስልክ መስመር 6922 በመደወል ጥቆማ በመስጠት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚችሉ ቢሮው አሳውቋል።
ሕገ-ወጥ ተግባራት ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የሕግ ተጠያቂነትንም እንደሚያስከትሉ ኃላፊዋ አስጠንቅቀዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: