ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትገለል የተጠነሰሰው ሤራ በድንገተኛ አጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን፣ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎች ተቀናጅተው የሀገራችንን እውነት በአደባባይ የዘረፉበት ነው።
ኢትዮጵያ በባንዳዎች እና ባዳዎች በአደባባይ የተነጠቀችው እውነት የአሁኑ እና ቀጣዩ ትውልድ የጂኦፖለቲካዊ መብቱን በጋራ እንዲጠይቅ የሚያነቃው ሕያው እውነታ ነው።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እና በነዳጅ ምርቶች ራሷን ለመቻል በአሰብ ወደብ ላይ የገነባችው ግዙፉ የነዳጅ ማጣሪያ የዚህ ስልታዊ ዝርፊያ ዋነኛ ሰለባ ነበር።
በጥር ወር 1956 ዓ.ም ተጀምሮ በጥቅምት 1960 ዓ.ም የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት፣ በወቅቱ በሶቭየት ኅብረት የቴክኒክ ድጋፍ እና ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ በጀት የተገነባ የሀገራችን የመጀመሪያው የከባድ ኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ነበር፡፡
በማስፋፊያ የዕድገት ጊዜያት የማጣራት አቅሙ ከፍ እያለ መጥቶ በዓመት እስከ 800 ሺህ ሜትሪክ ቶን ደርሶም ነበረ፡፡
በግንቦት 1983 ዓ.ም አሰብ ለሻዕቢያ ሲሰጥ ይህ የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብትም አብሮ ተነጠቀ፡፡
ምንም እንኳ በወቅቱ የጋራ አጠቃቀም ስምምነት ተሞክሮ ነበር ቢባልም፣ የጋራ የሆነውን ሀብት የግሉ ለማድረግ ወስኖ የተነሳው የኤርትራ መንግሥት የጋራ ተጠቃሚነት መርሁን ሆን ብሎ አደናቀፈ፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ ላብ በገነባችው መሠረተ ልማት ላይ የተጋነነ የነዳጅ ማጣሪያ ክፍያ በመጫኑ እና ጊዜ ያለፈበትን ማጣሪያ ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ እንድታድስ በመጠየቁ፣ ማጣሪያው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ውስጥ ወድቆ በ1989 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ተደረገ፡፡
የተፈጸመው ዝርፊያ በመሠረተ ልማት ላይ ብቻ አላበቃም፡፡ ከኤርትራ መገንጠል በፊት የአሰብን 70 በመቶ ሕዝብ ይሸፍኑ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በወደብ፣ በነዳጅ ማጣሪያ እና በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዘርፎች ከተማዋን ሲያንቀሳቅሱ የኖሩ የጀርባ አጥንቶች ነበሩ፡፡
ነገር ግን መገንጠሉን እና የድንበር ጦርነቱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያፈሩትን ሀብት ተነጠቁ፡፡
ይህም ሳይበቃ በግዞት ካምፖች ታስረው አካላዊ ድብደባ እየደረሰባቸው፣ የጥርስ ወርቃቸው ጭምር ያለ ርህራሄ እየተነቀለ በባዶ እጃቸው ተባረሩ፡፡
ይህ በዜጎች ላይ የደረሰ ሰብአዊ ቀውስ ብቻ አልነበረም። በወቅቱ ከ130 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚገመት የኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ንብረት እና አስመጪ ዕቃዎች በአሰብ ወደብ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ተወረሱ።
የዚህን ስልታዊ የንብረት ዘረፋ እና ሕገ-ወጥ ማፈናቀል እውነታ ዓለም አቀፉ የካሳ ኮሚሽን (EECC) ባደረገው ጥልቅ ምርመራ አረጋግጦ በኤርትራ ላይ የካሳ ውሳኔ አስተላልፏል።
ሆኖም በወቅቱ በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የነበረው እና የኤርትራ አፈ ቀላጤ በመሆን ሲያገለግል የነበረው የውስጥ ኃይል ይህን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ ጉዳይ መነሻ አድርጎ ለዜጎቹ እና ለሀገሩ የባሕር በር መብት ከመቆም ይልቅ፣ ግፍ የተፈጸመባቸውን ኢትዮጵያውያን እንደ ወንጀለኛ ሲቆጥር ታይቷል።
ከዚህ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ቀውስ ባሻገር የባሕር በር መነጠቁ አንድ የሆነውን የአፋር ሕዝብ ታሪካዊ አንድነት የገነጠለ ትልቅ ሤራ ነው።
የአፋር ሕዝብ የራሱ የሆነ ወጥ ባህል፣ ቋንቋ እና መሬት ያለው ማኅበረሰብ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማነቅ በፈጠሩት ሤራ ለሁለት እንዲከፈል ተገደደ።
ተፈጥሯዊ የጀርባ አጥንቷ ከሆነው የኢትዮጵያ አፋር መሬት ተነጥላ የተከለለችው አሰብ፣ ሕዝቡ ከባሕር ጋር ያለውን ቀጥተኛ ታሪካዊ ግንኙነት እንድታጣ ተደረገች፡፡
ወትሮውንም ያለ ባለቤቷ የማያምርባት አሰብ ባለፉት 35 ዓመታ ዛሬ ከሕዝቧም ከልማቷም ተለይታ ሤረኞቹ እንዳለሙላት ባይተዋር የግመል መጠጫ ብቻ ሆና ቀርታለች።
የዛሬው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መነሻም ይኸው ታሪካዊ ስህተት፣ የተጠነሰሰው ሤራ እና የሕዝብ መከፋፈል ነባራዊ ሀቅ ነው።
ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር በመቅረቷ ምክንያት ብቻ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአገልግሎት ክፍያ እያጣች ትገኛለች።
ለዚህም ነው ሁልጊዜም የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የቀይ ባሕር መዳረሻዋ እንዲመለስላት እየጠየቀች ያለችው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ይህን እውነታ በግልጽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ በ2010 ዓ.ም ከኤርትራ ጋር ተፈጥሮ በነበረው የሰላም ስምምነት ማግሥት ኢትዮጵያ ነባሩን የአሰብ መሠረተ ልማት በራሷ ወጪ አድሳ እና አልምታ ሁለቱም ሀገራት በጋራ እንዲጠቀሙ እና ወደቡን የጋራ የኢኮኖሚ ሞተር ለማድረግ ያደረገችውን ልባዊ ጥረት የኤርትራ መንግሥት በሩን በመዝጋት አደናቅፎታል።
ታሪካዊ ስህተቶች መታረም ያለባቸው በመነጠል እና በመነጠቅ ሳይሆን፣ የጂኦፖለቲካ እውነታዎችን በመቀበል፤ በአፋር ሕዝብ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስር ላይ የተመሠረተ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ስምምነትን በማጠናከር ነው።
አዲሱ ትውልድ ይህንን የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ሤራ በሚገባ ተረድቶ፣ ለሐዘን ሳይሆን ለሀገር ሉዓላዊነት መብት እና ለጋራ ብልጽግና በአንድነት ሊቆም ይገባል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: