ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነች ዲጂታላይዝ ሀገር ለመፍጠር እየተሰራ ነው ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዘመናዊ እና ዲጂታላይዝ ፣በፈጠራ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር የተቋቋመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የአሰራር ሂደቱን ለማዘመን 500 አገልግሎቶችን በዛሬው ዕለት ይፋ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወረቀት የፀዳ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እየሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በሌሎች መስሪያ ቤቶችም ከወረቀት ንኪኪ ውጪ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ሰፊጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
ዲጂታላዝ የሆነ አሰራር ሲገነባ ግልጸኝነት፣ የጊዜ እና የሀብት ቁጠባ እንደሚኖርም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ከበጀቷ ከ40 ቢሊዮን በላይ ለወረቀት ግዢ የምታወጣ ሲሆን ከወረቀት ነፃ ዲጂታላዝ አሰራር ሙሉ በሙሉ ከተካች ይህንን ወጪ እንደምትቀንስም ነው ያነሱት።
በመስሪያ ቤቱ የሚሰሩ ሰራተኞችን ለመደገፍ በተለይ ለሴቶች በርካታ ስራዎች ስለመሰራታቸውም ነው የጠቀሱት፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በቅርቡም የመሶብ የአንድ አገልግሎት ተገንብቶ ስራ ላይ መዋሉንም አስታውሰዋል፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ ተቋማት ዘምነው ዲጂታል የሆነ አሰራር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለሙት ቴክኖሎጂዎች ስራ ቀልጣፋ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማትና የስራ ስምሪት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት