የሲዳማ ክልል በ2018 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ 3.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ ከሦስት ሚሊዮን 280 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ክልሉን የጎበኙ ሲሆን፣ ይህ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ35 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
የሲዳማ ክልል የባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ እንደገለጹት፣ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪዶር ልማት ስራዎች እና የቱሪስት መዳረሻዎችን የማሻሻል ጥረቶች ለዚህ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በተለይም በሀዋሳ ከተማ ከጥቁር ውሃ እስከ ታቦር ተራራ የሚዘረጋው የ12 ኪሎ ሜትር የሀይቅ ዳርቻ ልማት ስራ፣ የወንዶ ገነት ፍል ውኃ እንዲሁም የይርጋለም አካባቢ የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ እያሸጋገሩት ይገኛል።
በቱሪዝም ዘርፉ በተመዘገበው ውጤት በበጀት ዓመቱ ብቻ ለ1 ሺህ 200 ዜጎች ቋሚ፣ ለስድስት ሺህ የሚሆኑ ወገኖች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።
አቶ አበበ አክለውም፣ ክልሉ የቱሪዝም መዳረሻነቱን ይበልጥ ለማጠናከር አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማት እና ያሉትን የመሰረተ ልማት ውስንነቶች የመፍታት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: