Search

የውኃ ዋስትና እና የንፅህና አምድ፡ የኢትዮጵያ የተቀናጀ ሀገር በቀል ስትራቴጂ

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 50

ደህንነቱ የተጠበቀ ውኃ፣ ሳኒቴሽን እና የግል ንፅህና ለሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎትና ሰብአዊ መብት ነው። በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተማ መስፋፋት እና የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የኢነርጂ ዘርፎች የውኃ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ለዓለም ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2026 የዘላቂ ልማት ግቦች (SDG 6) ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ከሦስቱ የዓለም ሕዝብ አንዱ ከፍተኛ የውኃ ውጥረት ባለበት አካባቢ ይኖራል።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት በመረዳት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትኩረት እያከናወነችው ያለው ዘርፈ-ብዙ የልማት ስራ ስልታዊ ፋይዳው የላቀ ነው።

የዓለም አቀፉ የሳኒቴሽን ቀውስ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል። በ2024 መረጃ መሰረት 3.4 ቢሊዮን ሕዝብ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳኒቴሽን አገልግሎት ይጎድለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ እንደሚጠይቀው፣ በ2030 ግቦችን ለማሳካት አሁን ያለው የዕድገት ፍጥነት በሳኒቴሽን ረገድ 6 እጥፍ፣ በግል ንፅህና ረገድ ደግሞ በእጥፍ ማደግ አለበት።

ይህንን የፍጥነት ማሻሻያ ጥሪ በተግባር ለመመለስ በኢትዮጵያ የተጀመረው የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ዘመቻ ወሳኝ ምላሽ ነው። ዘመቻው ማኅበረሰቡንና የግሉን ዘርፍ በማስተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

ይህ እንቅስቃሴ የሜዳ ላይ መፀዳዳትን በማስቀረት የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል እና ዓለም አቀፍ የንፅህና ግቦችን በፍጥነት ለማሳካት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

የተቀናጀ የውኃ አስተዳደርን ለመተግበር በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዘርፈ-ብዙ ቅንጅትን በተግባር የመለሰ ስትራቴጂ ነው።

የኮሪደር ልማቱ የመንገድ፣ የውኃ መስመር፣ የፍሳሽ ማስወገጃ እና የአረንጓዴ ስፍራዎችን ግንባታ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ በማቀናጀት ቀደም ሲል የነበረውን የተናጠል አሰራር ሰብሯል።

ይህም በቧንቧዎች መሰበር የሚባክነውን የንጹሕ ውሃ መጠን በመቀነስ የውሃ አጠቃቀም ውጤታማነትን ያሳድጋል። የገጠር ኮሪደር ልማት ንጹሕ መጠጥ ውሃን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እና የጤና ተቋማትን በአንድ ላይ በማቅረብ በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የልማት ልዩነት በማጥበብ ፍትሃዊነትን ያረጋግጣል።

በምድር ላይ ያለው ንጹሕ ውሃ እጅግ አናሳ በመሆኑ የውሃ ምንጮችን መጠበቅ ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ስራ ወንዞችን በማጽዳት፣ ዳርቻዎቻቸውን በማስዋብና የፈሳሽ ቆሻሻዎችን በመቆጣጠር የላይኛውን የውኃ አካላት ጥራት ይጠብቃል።

ይህ ስራ የውሃ ማጣሪያ ወጪን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥ የውኃ እጥረትን እያባባሰ መምጣቱን በመረዳት የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለኢትዮጵያ የውሃ ዋስትና የረጅም ጊዜ መፍትሄ ነው።

ችግኞችን መትከል የዝናብ ውሃ ወደ ከርሰ-ምድር እንዲሰርጽ በማድረግ የውኃ መጠንን ከፍ ያደርጋል፤ የአፈር መሸርሸርን በመግታት ደግሞ ለታላላቅ ግድቦቻችን የውሃ የመያዝ አቅም አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ጉዟችንን ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስ ሁሉን አቀፍ ኢንቨስትመንት፣ ዘርፈ-ብዙ ቅንጅት እና የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር አቀራረብ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለቻቸው የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ዘመቻ እና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች በትክክለኛው የዓለም አቀፍ መርህ መስመር ላይ ያሉ ስትራቴጂያዊ ተግባራት ናቸው።

እነዚህን ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የወጣቶችንና የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበት፣ በውሃ ምርምር ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና የተቀናጁ መሠረተ-ልማቶችን በተቋም ደረጃ በማስቀጠል አገራችን የ2030 የውሃና ንፅህና ግብን በላቀ ደረጃ ለማሳካት የምታደርገውን ጉዞ ማፋጠን ይገባታል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: