Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀድሞው የኳታር አሚር ሼክ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ታኒ በማረፋቸው የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 52

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በራሳቸው፣ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ለኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ፣ ለሀገሪቱ መንግሥትና ለወንድም የኳታር ሕዝብ ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ "አባት ኤሚር"፣ ሼክ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ታኒ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈን፣ ለውይይትና ለድርድር መሠረት በመጣል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጥበበኛ መሪ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በተለይም ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ይሰጡ እንደነበርና የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ከመጀመሪያው ሒጅራ ጀምሮ የቆየ ጥልቅ ታሪካዊ መሠረት እንዳለው በተደጋጋሚ ይገልጹ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ደግሞ ለሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነትና ለተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች መሠረት የጣለ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት በአሁኑ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ መሪነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ በሞት ለተለዩት መሪ ዕረፍትን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለኳታር ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: