Search

ታሪክ ለመሥራት 90 ደቂቃ ብቻ! የሉሲዎቹ ወሳኝና ታሪካዊ ፍልሚያ ዛሬ በስታዲየም

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 78

ዛሬ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በታሪካዊ ፍልሚያ ይሞቃል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞሮኮ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከዛምቢያ ጋር ወሳኝ የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል።

በዛምቢያ በተካሄደው የመጀመሪያ ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፈው የነበሩት ሉሲዎቹ፣ ዛሬ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ታሪክ ለመስራት በቁጭትና በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ ይገኛሉ።

ወደ ዓለም ዋንጫው ለመሸጋገር ዛሬ በሚያደርጉት ጨዋታ ዛምቢያን በድምር ውጤት መብለጥ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለዚህም በጨዋታው አንድ እና ከዚያ በላይ ግብ አስቆጥሮ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ራውዳ አሊ በልጆቻቸው ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው በመግለጽ፣ የመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት የፈጠረውን ቁጭት በዛሬው ድል እንደሚካክሱት ተናግረዋል።

አሰልጣኟ አክለውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር በመጥቀስ፣ "ቀሪዋን 90 ደቂቃ በስታዲየም ተገኝታችሁ ድጋፍ ስጡን" ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የቡድኑ አምበል ምህረት ወሰኑ በበኩሏ "በእልህና በቁጭት በሀገራችን እና በደጋፊያችን ፊት ውጤት ይዘን ለመውጣት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን" ስትል የቡድኑን የአሸናፊነት ስሜት ገልጻለች።

ቀን 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄደው ይህ ወሳኝ ጨዋታ መላው ስፖርት ወዳድ ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው ጨዋታ ሆኗል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉሲዎቹ ድልን እንዲመኝና በስታዲየም በመገኘትም ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል። እስኪ ለቡድናችን ድልን በአንድነት እንመኝላቸው? ሉሲዎቹ በታሪክ መዝገብ ላይ ስማቸውን ያስፈራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: