በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ በተካሄደው 32ኛው የፓርላማ የመረጃና ደህንነት ፎረም ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የፓርላማ አባላት፣ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎች የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።
እንግዶቹ በመታሰቢያው የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ሰነዶችን፣ ፎቶግራፎችንና ዘመናዊ የዲጂታል ማሳያዎችን በመመልከት ስለ ዓድዋ ድል ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ዓድዋ የአፍሪካውያን ጀግንነት፣ አንድነትና ጽናት መገለጫ መሆኑን የጠቀሱት ጎብኝዎቹ፣ ሙዚየሙ የታሪክ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለመላው ዓለም የተስፋ ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ የታሪክ ቅርሶችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለትውልድ ለማስተላለፍ የተደረገውን ጥረትና የመታሰቢያውን ዘመናዊ አደረጃጀት አድንቀዋል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም ኢትዮጵያ ከመቶ ሰላሳ ዓመታት በፊት ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ታሪካዊ ምሳሌ ከመሆኗም ባለፈ፣ ዛሬም በአንድነትና በቁርጠኝነት ወደ ቀጣይ የልማትና የእድገት ምዕራፍ እየገሰገሰች መሆኗን መናገራቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ ፎረም ላይ የመረጃ ልውውጥን ማጠናከር፣ ፓርላማዊ ቁጥጥርን ማሳደግ፣ በደህንነት ዘርፍ ያለውን ዓለም አቀፍ ትብብር ማጎልበት እንዲሁም ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊና ክልላዊ የፀጥታ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: