Search

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ዜጎቹ ደኅንነት፣ ጥበቃና የቆንስላ ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 114

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ዜጎቹ ደኅንነት፣ ጥበቃና የቆንስላ ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የሚኒስቴሩ መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያውያንን ሁኔታ በተለይም ደግሞ የሕግ ሒደትና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ወገኖች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት መሥራቱን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ዜጎቹ ደኅንነት፣ ጥበቃና የቆንስላ ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በሚገኙ ዜጎች ጉዳይም መንግሥት በከፍተኛ አመራሩ በኩል ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተከታታይ ውይይቶች አድርጓል።

በተጨማሪም በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በጅዳ በሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል አማካኝነት፥ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ሰብዓዊ ምሕረት እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ፣ የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግና ተገቢው መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር ያለውን ውይይት አጠናክሮ ቀጥሏል።

እነዚህ ቀጣይነት ያላቸው የዲፕሎማሲ እና የቆንስላ ጥረቶች በሰብዓዊነት ረገድ አዎንታዊ ውጤቶችን አስገኝተዋል።

እስከ አሁን ድረስ በአጠቃላይ 1 ሺህ 971 ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ካደረጉት የንጉሣዊ ምሕረት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥትም እነዚህን ዜጎች ወደ አገራቸው በተከታታይ በረራዎች እየመለሰ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ ይህንን ሒደት በቆንስላና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብርና የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ይገነዘባል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንን ጥቅሞች፣ መብቶችና ደኅንነት ለመጠበቅ ያሉትን የዲፕሎማሲና የቆንስላ አማራጮች ሁሉ መጠቀሙን የሚቀጥል ሲሆን፥ ዜጎቹን በሚመለከቱ ቀሪ ጉዳዮች ላይም ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: