Search

ከዕርዳታ እህል ጥገኝነት ወደ አህጉራዊ ኩራት፡ የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትና የታሪክ ስብራት እመርታ

ሰኞ ነሐሴ 18, 2018 38

ኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙና ሰፊ የሚታረስ የመሬት ሀብት እንዲሁም ምቹ ሥነ-ምህዳር ያላት አገር ብትሆንም፣ ለዘመናት መሬቷን በአግባቡ ማልማትና ምርታማነቷን ማሳደግ ሳትችል ቆይታለች።

ዘመናዊ አሠራር ባለመዘርጋቱ ምክንያት ለዜጎቿ ከውጭ ስንዴ ሲሰፈርላት የኖረችበት የተረጂነት ታሪክ የተጫናት አገር ሆና ኖራለች።

ይሁን እንጂ ባለፉት የሀገራዊ ለውጥ ዓመታት በተወሰዱ መዋቅራዊ የፖሊሲ እርምጃዎችና በተካሄዱ የልማት ንቅናቄዎች፣ ከከፋ የውጭ ጥገኝነትና ከዕርዳታ ጠባቂነት በመውጣት የምግብ ሉዓላዊነቷንና የኢኮኖሚ ነፃነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችላትን የብልፅግና ጉዞ ጀምራለች።

በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ ትልቁን የለውጥ ምዕራፍ የከፈተውና ጨዋታ ቀያሪ የሆነው ስትራቴጂ፣ ስንዴን ከመደበኛው የክረምት ወቅት በተጨማሪ በበጋ ወቅት በመስኖ በቆላማና በደጋማ አካባቢዎች በስፋት ማልማት መቻሉ ነው።

ቀደም ሲል በየዓመቱ እስከ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዢ እና በዕርዳታ ከውጭ የምታስገባ የነበረ ሲሆን፣ ለዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማውጣቷም በላይ በንግድ ሚዛኗ፣ በዕዳ ጫናዋና በገፅታዋ ላይ አሉታዊ ጥላ ሲያሳርፍ ቆይቷል።

ይህን የታሪክ ስብራት ለመጠገን በተከናወኑ መጠነ-ሰፊ ሥራዎች፣ በስፋት የተተገበረው የኩታ-ገጠም እርሻ ስልት አርሶ አደሮች መሬታቸውን አጣምረው ዘመናዊ ማዳበሪያን፣ ምርጥ ዘርንና ቴክኖሎጂን በጋራ እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ትራክተርና ኮምባይነር ያሉ የሜካናይዜሽን መሣሪያዎች አቅርቦት በማደጉ የስንዴ ምርት በዓመት 240 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መድረስ ችሏል።

ይህ አስደናቂ እመርታ የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር የሚያስገኝ አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥሯል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን በገጠር ብቻ ተወስኖ አልቀረም፤ ይልቁንም ለውጡን ወደ ከተሞች በማሸጋገር የከተማ ግብርናን በስፋት ማለማመድ ተችሏል።

"ምግቤን ከደጄ" በሚል መሪ ቃል በከተሞች በተከናወኑ የጓሮ፣ የህንፃ ጣሪያና የአነስተኛ ቦታዎች ልማት፣ ዜጎች አስፈላጊውን ንጥረ-ነገር ከራሳቸው ግቢ እንዲያገኙ ማስቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ አያሌ ወጣቶችና ሴቶች በተቋማት ተቀጥረው ከመሥራት ይልቅ በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዲያመቻቹ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በመሆኑም በአርሶ አደሩ ማሳና በከተማ ነዋሪው ግቢ የተመዘገበው ይህ ዘርፈ-ብዙ የግብርና እመርታ ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ ሀገራችንን ከውጭ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻልና ወደተሟላ የምግብ ሉዓላዊነት ያሸጋገራት ታላቅ የአስተሳሰብና የታሪክ ለውጥ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: