Search

በኦሮሚያ ክልል የ2018 ዓ.ም የመንግሥት እና የፓርቲ ስራ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀመረ

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 164

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ወራት የተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎችን አፈጻጸም ለመገምገም ያለመ ሰፊ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩ ክልሉ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማጠናከር እና ያጋጠሙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን በማረም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲ አባላት እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ በዋናነት በሕዝብ ተጠቃሚነት፣ በሰላም እና ደኅንነት፣ በመሰረተ-ልማት እና በገቢ አስባሰብ ዙሪያ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት ነው።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሸመልስ አበዲሳ አመራሩ ባለፉት ጊዜያት በቁርጠኝነት መስራቱን ጠቁመዋል።

በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን አመራሩ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በየዘርፉ የተመዘገቡት ስኬቶችም የዚሁ ቁርጠኝነት ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሸመልስ አያይዘውም በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ በነበሩት ጊዜያት በዕቅድ ተይዘው የተንጠባጠቡ እና ያልተሟሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፣ በክልሉ በርካታ አበረታች ስኬቶች ቢመዘገቡም አሁንም በዞኖች መካከል ያለውን የአፈፃፀም ልዩነት ማጥበብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሳዳት መሀመድሳኒ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: