Search

የዓለም አቀፍ የቤት ኪራይ ደንብ ተሞክሮ - የአሜሪካ የኪራይ ቁጥጥር ስልቶች ለኢትዮጵያ ምን ያስተምራሉ?

ሰኞ ሐምሌ 06, 2018 150

የከተሞች መስፋፋት እና የኮሪደር ልማት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በከፍተኛ ሁኔታ በሚቀይሩበት ወቅት፣ የቤት ኪራይ ውል እና የዋጋ ቁጥጥር ሥርዓትን በሕግ መደገፍ የዜጎችን ማኅበራዊ ኑሮ ለማረጋጋት ወሳኝ እርምጃ ነው።

በዚህ ረገድ በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነችው አሜሪካ የምትከተለው የቤት ኪራይ ሕግ እና ተሞክሮ፣ የመሬት ባለቤትነት መብትን ከዜጎች የመኖሪያ ዋስትና ጋር እንዴት ማመጣጠን እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው።

በአሜሪካ የቤት ኪራይ ውል ተራ የውል ሰነድ ሳይሆን፣ በፌዴራል እና በግዛት ሕጎች በጥብቅ የሚመራ የሲቪል መብት ነው።

እንደ ኒውዮርክ፣ ሳን ፍራንሲስኮ እና ሎስ አንጀለስ ባሉ ግዙፍ የንግድ ከተሞች ውስጥ ተግባራዊ የሚደረገው የኪራይ ቁጥጥር ሕግ፣ የቤት አከራዮች በየዓመቱ የኪራይ ዋጋን በዘፈቀደ እንዳይጨምሩ ገደብ ይጥላል።

የኪራይ ጭማሪው የሚወሰነው በየዓመቱ በከተማዋ የኑሮ ውድነት መለኪያ እና በልዩ የኪራይ ቦርድ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ነው።

ይህ አሠራር ተከራዮች በአከራዮች የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ከቤት የመፈናቀል ስጋት እንዳይገጥማቸው ያደርጋል።

አከራዩ የቤቱ ባለቤት ቢሆንም፣ የኪራይ ውል ከተፈጸመ በኋላ ተከራዩ በቤቱ ውስጥ የማያወላውል የመኖር ሕጋዊ መብት ይኖረዋል።

በዚህም መሠረት አከራዩ አስቀድሞ ሳያሳውቅ ወይም ሕጋዊ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ወደ ተከራየው ቤት መግባት አይችልም፤ ድርጊቱም በሕግ የሚያስቀጣ ነው።

በተጨማሪም በአብዛኛዎቹ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ቤቶች ውስጥ፣ ተከራዩ የኪራይ ውሉ ሲያልቅ ውሉን የመቀጠል ቀዳሚ መብት አለው። አከራዩ ሕጋዊ እና አሳማኝ ምክንያት ካላቀረበ በስተቀር ተከራይን ውል አላድስም በማለት ማስወጣት አይፈቀድለትም።

በአከራይ እና ተከራይ መካከል አለመግባባት ሲፈጠርም ጉዳዩ የሚታየው ለዚሁ ተብሎ በተቋቋሙ ልዩ የቤት ፍርድ ቤቶች ነው።

ይህ የአሜሪካ ተሞክሮ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ፈጣን የከተማ ዕድገት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት ትልቅ እውነታን ያስጨብጣል።

የቤት ኪራይ ውልን ማዘመን እና የዋጋ ጭማሪን በሕግ መግታት፣ የቤት አከራዮችን ተገቢ ጥቅም ሳይነካ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በከተሞች ውስጥ ተረጋግተው እንዲኖሩ ያደርጋል።

የከተማ አስተዳደሮች የቤት ኪራይ ሕግን በማጠናከር፣ ከአከራይ እና ተከራይ የሚጠበቀውን ግዴታ እና መብት ግልጽ ማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ከተሞች ማኅበራዊ መረጋጋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: