በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች አልፈዋል። ጦርነቶች ተካሂደዋል፣ መንግሥታት ተቀይረዋል፣ ትውልዶችም ተፈራርቀዋል።
ለዘመናት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶች ሲፈቱ የኖሩት በጠብመንጃ አፈሙዝ ነበር፤ ሹክቻዎች ሲፈጠሩ መፍትሔ ፍለጋ የምንሮጠው ወደ ጦር ሜዳ እንጂ ወደ የጋራ መመካከሪያ ጠረጴዛ አልነበረም።
የኢትዮጵያ ልጆች ያለምንም አግላይነት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የልባቸውን አውጥተው ለመነጋገር እና በመፃዒ ዕድላቸው ላይ ለመመካከር የወሰኑበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
ይህ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ፈጽሞ አዲስ ምዕራፍ ነው።
አለመግባባቶችን በጠብመንጃ አፈሙዝ፣ በጉልበት፣ በግጭት ወይም በዝምታ የማለፍ የቆየ ልማዳችንን ሰብረን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሰናል።
ይህ የሀገራችን ጉዞ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ልዩነቶቻችንን እንደ ውበት ተቀብለን፣ ኢትዮጵያ ከገጠማት ዘርፈ-ብዙ ፈተና እንድትወጣ እና ጠንካራ ሀገራዊ ሥነ-ልቦና ለመገንባት የምናደርገው ታሪካዊ ጅምር ነው።
ወሳኙ የታሪክ ቀጠሮ፦ ይህ ትውልድ በጉጉት የሚጠብቀው እና ወሳኝ የሆነው የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ ሊካሄድ የቀሩት 2 ቀናት ብቻ ናቸው።
ታሪካዊው ክስተት ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ይጀምራል። ይህች ቀን በሀገራችን የታሪክ መዝገብ ላይ አዲስ የሰላም እና የመግባባት ማዕዘን የምትተክልበት ትሆናለች።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወሳኝ ምዕራፍ፣ ያለፈውን የሻከረ ቁስል የምንጠግንበት እና የወደፊቱን የጋራ ራዕይ በጋራ የምንቀርጽበት ነው።
የኢትዮጵያ ልጆች በልዩነታቸው ውበት፣ በአንድነታቸው ጉልበት ታሪክን በአዲስ መልክ ሊጽፉ እነሆ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተዋቸዋል!
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: