በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሽግግር ውስጥ የምታልፍ ሀገር ሁልጊዜም ቢሆን የመንገዷን አቅጣጫ የሚጠቁሙ መብራቶች ያስፈልጓታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የሀገራችን ወቅታዊ ፈተናዎች እና የወደፊት ተስፋዎች የሚቃኙ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል “ሀገራችን የጎደላት ልማት ነው፤ የጎደላት ብልፅግና ነው፤ የጎደላት መደማመጥ እና መከባበር ነው፤ ከታሪክ መልካም መልካሙን ወስዶ የቀረውን እየሞሉ ለልጆቻችን የተሻለ ሀገር ማስረከብ ያስፈልጋል” የሚለው መልዕክታቸው ይህን ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሀገራችን የጎደላት ልማት ነው፤ የጎደላት ብልፅግና ነው” ሲሉ የችግሮቻችንን ስረ-መሰረት በግልፅ አስቀምጠውታል።
ለብዙ ዘመናት በድህነት እና በግጭት አዙሪት ውስጥ የቆየች ሀገር ወደፊት መራመድ የምትችለው የዜጎቿን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ስትችል ነው።
ለዚህም የመደመር መንግሥት እያከናወኗቸው የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መንገዶች፣ ንፁህ መጠጥ ውኃ፣ ኃይል እና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ይህንን የዜጎች ፍላጎት ለማሟላት እየተደረጉ ያሉ ተግባራት ናቸው።
በዚሁም ልማት እና ብልፅግና የሚታሰቡት ሰላም እና መረጋጋት ሲኖር ነው። ሰላም ደግሞ የሚመጣው ከልብ ከመደማመጥ እና ከመከባበር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ምህዳር ክፍተት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
እውነተኛ መደማመጥ ባለበት ቦታ ልዩነቶች የውይይት ማበልፀጊያ እንጂ የትርምስ መንስኤ አይሆኑም።
አንዳችን ሌላችንን ማክበር ስንችል ሀገራዊ አንድነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። ይህ ካልሆነ ግን የምንገነባው ልማት በግጭት መና ሆኖ የመቅረት ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ ረጅም እና ኩሩ ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም ያ ታሪክ ግን ሙሉ በሙሉ እንከን አልባ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት የታሪክ እስረኛ መሆን ግን የለብንም።
ይልቁንም መልካም መልካሙን በመውሰድ የጥንቱን የአንድነት፣ የጀግንነት፣ በጋራ የመኖር እና የባህል እሴቶቻችንን ጠብቆ ማስቀጠል ያስፈልጋል።
እንዲሁም በአባቶቻችን ዘመን የነበሩ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የእኩልነት ክፍተቶችን ዛሬ ላይ እያረሙ እና እየሞሉ መሄድ ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው።
የዚህ ሁሉ ጥረት የመጨረሻ ግብ ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ማስረከብ ነው። እኛ ዛሬ የምንከፍለው መስዋዕትነት፣ የምናሳየው ትዕግስት እና የምንገነባው የልማት ሥራ ነገ ለሚመጣው ትውልድ የሚተርፍ ቅርስ ነው።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት እያንዳንዱ ዜጋ፣ ምሁር፣ ፖለቲከኛ እና አመራር ራሱን እንዲጠይቅ የሚያስችል የህሊና ጥያቄ ነው።
"እኔ ለሀገሬ ልማት፣ ለዜጎች መከባበር እና ለመግባባት ምን አያበረከትኩ ነው?" ብሎ መጠየቅ የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: