Search

የባሌ ተራሮች፡ የኢትዮጵያ የሕይወት ማማ እና የዓለም የተፈጥሮ ቅርስ

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 68

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 38 እስከ 7 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በነበረ የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ የተፈጠረ እና አስደናቂ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለው በረዷማ ፓርክ ነው።

በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ይህ ፓርክ ከባሕር ወለል በላይ 1 ሺህ 800 እስከ 4 ሺህ 385 ሜትር ከፍታ ባላቸው የመሬት አቀማመጦች የተሸፈነ ሲሆን፣ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱም 2 ሺህ 150 እስከ 2 ሺህ 220 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

በፓርኩ ውስጥ 4 ሺህ 385 ሜትር ከፍታ ያለው የሀገራችን ሁለተኛው ረጅሙ ተራራ የሆነው ቱሉ ዲምቱ፣ ሰፊው የሰናቴ አፍሮ-አልፓይን ፕላቶ፣ ምስጢራዊው የሃረና ደን እና ልዩ የድንጋይ ቅርጽ ያለው የራፉ ድንጋይ ደን ይገኛሉ።

ፓርኩ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል ከፍተኛ የውኃ ምንጭ በመሆኑ "የውኃ ማማ" በመባል ይታወቃል።

በአካባቢው በሚፈጠረው ከፍታ-አቀፍ ዝናብ ምክንያት ፓርኩ በዓመት 600 እስከ 1 ሺህ 400 ሚሊሜትር ዝናብ የሚያገኝ ሲሆን፣ 40 በላይ የሚሆኑ ወንዞች እና ምንጮች መነሻ ነው።

እነዚህ ወንዞች በታችኛው ተፋሰስ ለሚኖሩ ሚሊዮኖች ለሕይወት፣ ለግብርና እና ለእንስሳት መጠጥ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ፓርኩ አህጉራዊ አካባቢያዊ ውህደትን ለመጠበቅ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በብዝኃ ሕይወት ረገድ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የሌለው የሕይወት መቅደስ ነው። ፓርኩ አራት ዋና ዋና የዕፅዋት እና እንስሳት ቀጣናዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም የገይሳይ ሣር ምድር፣ የፅድና ቆሶ ደን፣ የሰናቴ አፍሮ-አልፓይን እና የሃረና ደን ናቸው።

በውስጡም 79 የሚያህሉ አጥቢ እንስሳት፣ 160 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች እና በርካታ የዕፅዋት ዓይነቶች ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል በዓለም ላይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ቀይ ቀበሮ፣ ንያላ፣ ግዙፉ የምድር ዓይጥ እና የባሌ ዝንጀሮ የሚገኙበት ልዩ ሥነ-ምህዳር ነው።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች ሁለገብ የቱሪዝም አማራጮችን ያቀርባል። ፓርኩ ለእግር ጉዞ፣ ለካምፒንግ፣ ለፈረስ ጉዞ፣ ለአእዋፍ እና እንስሳት እይታ እንዲሁም በሃረና ደን ውስጥ ለዛፍ ላይ የእግር ጉዞ በጣም ተመራጭ ነው።

እንደ ባሌ ማውንቴንስ ሎጅ ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያዎች እና የማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ፓርኩ በዩኔስኮ የዓለም ተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ለሀገራችን ትልቅ የዲፕሎማሲ እና የቱሪዝም ድል ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አማካኝነት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ዓለም አቀፍ ማስተዋወቅ እና የመሰረተ ልማት ማሻሻያ ዕድሎችን አግኝቷል።

ይህም የጎብኚዎችን ቁጥር የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ከዓለም አቀፍ አጋሮች እንደ የፍራንክፈርት ዞኦሎጂካል ሶሳይቲ እና የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ፓርኩን ለመጠበቅ ዘመናዊ የጥበቃ ሥራዎችን በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

ከመጠን በላይ ከብት ማሰማራት፣ የሰው ሰፈራ እና በእንስሳት በሽታዎች የሚደቀኑ ስጋቶችን ለመከላከል ከተፋሰስ እንክብካቤ እና ከማኅበረሰብ አቀፍ ጥበቃ ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: