የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጫፍ እስከ ጫፍ የሀገሪቱን ሰፊ የአየር ክልል በንቃትና በትጋት የሚቃኝ፣ ፈፅሞ የማይደፈር የኢትዮጵያ ብሩህ አይን ነው! ይህ የሰማይ ላይ ንስር በደመና ስንጥቅ ውስጥ ሲያስገመግም፣ አየሩን ሰንጥቆ ሲያንዣብብና ድምፁ ምድሪቱን ሲያናውጥ ያለው ግርማ ሞገስ እጅግ የሚያስፈራ ነው።
ለጠላት ልብን የሚያርድ፣ የክፋት ሴራንና ትንኮሳን ገና በአየር ላይ እያለ የሚያመክን አስፈሪ ኃይል ሲሆን፤ ለወዳጅና ለወገን ደግሞ ወደር የለሽ የኩራት፣ የክብርና የሰላም ምንጭ ነው።
በጀግንነት፣ በቆራጥነትና በማያወላውል የሀገር ፍቅር የታነፀው ይህ የሰማይ ላይ ኃይላችን፣ ማንም እንደፈለገ የማይፈነጭበትን፣ ጠላት ቀና ብሎ ለማየት የሚሳቀቅበትን አስተማማኝ የሰማይ ላይ የብረት ምሽግ በተግባር ገንብቷል።
ሰማዩ ላይ እንደ ንስር በከፍተኛ ፍጥነት እየተምዘገዘገ፣ በጠላት ሰፈር ድንጋጤንና ሽብርን የሚለቀው ይህ የኢትዮጵያ ምሽግ፣ የዛሬዋን ታላቂቱን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በብረት ክንፎቹ አቅፎ በክብር ይዟል።
ይህ አስፈሪ ግርማ ሞገስ፣ ልዕልና እና ወታደራዊ አቅም የመጣው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ ተቋሙ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባደረገው እጅግ ጥልቅ፣ ስፋት ያለው እና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ሪፎርም ነው።
የአየር ኃይሉ ሪፎርም መሰረታዊ የእሳቤ ለውጥ (Paradigm shift) ያመጣ፣ ተቋሙን ከስረ-መሰረቱ የቀየረ ታሪካዊ ሽግግር ነው።
ኃይሉ ካረጀ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት እና ከባህላዊ የውጊያ ስልት ወጥቶ፣ የዘመኑን እጅግ የተራቀቀ የሚሊተሪ ሳይንስ ጥበብ የተላበሰ ዘመናዊ አደረጃጀትን ፈጥሯል።
አየር ኃይሉ ዛሬ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (UAVs)፣ ዒላማን ሳይስቱ በሚመቱ ዘመናዊ ሚሳኤሎች፣ በተራቀቁ የራዳር ኔትወርኮች እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂን ታጥቋል።
የቴክኒክ፣ የጥገና እና የኢንጂነሪንግ ክፍሎቹ ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በሳይንሳዊ አሰራር ተደራጅተው፣ የሰው ኃይሉ በከፍተኛ የብቃት ደረጃ የሰለጠነ ሆኗል።
የሪፎርሙ ስፋት ተቋሙን ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አላቆ፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህገ-መንግስቱ ብቻ የታመነ፣ ሁሉንም መስፈርቶች የጠበቀ ዓለም አቀፋዊ ጠንካራ ኃይል አድርጎታል።
የዛሬው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የውጊያ እና የቴክኖሎጂ ቁመና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እጅግ አስተማማኝ የሰላም እና የፀጥታ ዋስትና ሆኖ ተገምቷል።
ድንበራችንን ጥሶ፣ አየር ክልላችንን ጥሶ ለመግባት በምናቡ ለሚያልብ ወይም ደፍሮ ለሚሞክር ማንኛውም ትምክህተኛ ኃይል፣ የአየር ኃይላችን የሰማይ ንስሮች የሚሰጡት ምላሽ ቅፅበታዊ፣ የማያዳግምና አውዳሚ ነው።
በዘመናዊ እና በዩኒቨርሳል የሚሊተሪ እሳቤ የተገነባው ይህ ኃይል፣ ሌሊቱን እንደ ቀን ብሩህ አድርጎ የሚያይበት፣ በየትኛውም የአየር ፀባይ ውስጥ ዒላማውን በትክክል የሚመታበት፣ እና ጠላትን ሳይታይ አድኖ የሚያጠፋበት አስደናቂ ብቃት አለው።
አየር ኃይሉ ውጊያን ከመግጠም አልፎ፣ ጦርነትን ቀድሞ የማስቀረት (Deterrence) ግዙፍ አቅም ፈጥሯል።
ኢትዮጵያችን በአስተማማኝ የልማት ጎዳና ላይ ያለስጋት እንድትጓዝ፣ እንዲሁም ማንም በሀገራዊ ክብሯ ላይ ቅንጣት ታክል እንዳይደራደር፣ የሰማዩ ንስር ሌት-ተቀን ነቅቶ ይጠብቃታል።
ይህ በአዲስ መንፈስ እና በቴክኖሎጂ የታጠቀ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ወደር የለሽ ክብር፣ የልጆቿ መመኪያ፣ እንዲሁም የጠላት መቀበሪያ የመጨረሻ ጉድጓድ ነው።
አየር ኃይላችን በእርግጥም የሰማዩ ንስር፣ አሻግሮ የሚያይ የኢትዮጵያ ብሩህ አይን ሆኖ በክብር ያንዣብባል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: