Search

የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች ለዘመናት በጥብቅ መስተጋብር የተሣሠሩ የሀገር ግንባታ ዋልታዎች ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 74

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች በጋብቻ፣ በፖለቲካዊ ትሥሥር እና በባህላዊ መስተጋብር የተሣሠሩ የሀገር ግንባታ ዋልታዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱን ሕዝቦች የዘመናት አብሮነት እና አኩሪ ታሪክ በስፋት አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመናት መካከል አብሮ የኖረ፣ የተጋመደ እና የተዋለደ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በተለይም በአቀማመጥ እና በቁጥር ሰፊ ድርሻ ያላቸው የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች በባህላዊ ጋብቻ እና በፖለቲካ ጋብቻ እንዲሁም በባህላዊ የጉዲፈቻ ሥርዓት ለዘመናት በጥብቅ መስተጋብር ውስጥ ማለፋቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሸዋ እና የይፋት ሡልጣኔቶችን እንዲሁም የጎንደር፣ የየጁ እና የወረ ሂመኑ ሥርወ መንግሥታትን በታሪክ ማሳያነት አንሥተዋል።

በእነዚህ ረጅም ዘመናት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተፈጠሩት ሰፊ ውህደቶች ሕዝቦቹ አብረው ሲዘምቱ፣ ሲያለሙ እና አብረው ሲዋጉ መኖራቸውን በግልጽ እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከእነዚህ ሕዝቦች ውህደት ውጤት እንሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

አፄ ምኒልክን ያለ ራስ ጎበና፣ ራስ ጎበናንም ያለ አፄ ምኒልክ ማሰብ አይቻልም፤ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በእነዚህ ታላላቅ ሰዎች ውህደት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚኮሩበት የዓድዋ ድልም የዚሁ ውህደት ትልቁ ማሳያ መሆኑ ጠቅሰዋል። አፄ ምኒልክ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ እና ደጃዝማች ባልቻን የመሳሰሉ ጀግኖች ለአንዲት የከበረች ሀገር የጋራ ሕልውና በጋራ ዘምተው ያመጡት ድል መሆኑንም አብራርተዋል።

በሕዝቦች ደረጃም በፊውዳሉ ሥርዓት ላይ የተነሡት የጎጃም እና የባሌ ገበሬዎች አመፆች የሕዝቦቹን ተመሳሳይ የትግል ታሪክ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

እነዚህ ሕዝቦች ለዘመናት በጋራ ሲነግዱ፣ ሲጋቡ እና ሲዋሃዱ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ይህ የመዋሃድ እና አብሮ የመኖር ልምድ በሌሎች ብሔሮች ውስጥም በስፋት የሚታይ እና ለኢትዮ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: