ኢትዮጵያ ምድርን አረንጓዴ ለማልበስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት በአንድ ጀምበር ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየፃፈች ትገኛለች።
ሀገር አቀፉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የዘንድሮውን 8 ቢሊዮን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ለማሳካት ታስቧል።
ችግኞችን በመትከል የተጀመረው የሕዝብ ንቅናቄ በየዓመቱ በሐምሌ ወር በሚካሄደው የአንድ ጀንበር መርሐ ግብር ተሳትፎውና የተተከለው ችግኝ ቁጥር እያደገ መጥቷል።
የፊታችን ሰኞ "ተስፋን እንትከል" በሚል መርህ በሚካሄደው ታሪካዊ መርሃ ግብር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ሙሉ ዝግጅት ተጠናቋል።
ይህ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገራዊ መግባባት ለአብሮነትና ለማህበራዊ መስተጋብር መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ዜጎች ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰባስበው ችግኝ የመትከል ባህልን ማዳበራቸው "ከእኔነት ይልቅ የእኛ" የሚል አስተሳሰብ እንዲጎለብት ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ እንዲያድግና የጋራ ሀገር ባለቤትነት ስሜት እንዲጠናከር አድርጓል።
ሀገራችን በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለድርቅ ለጎርፍና ለተፈጥሮ አደጋዎች ስትጋለጥ የቆየች ቢሆንም ተፈጥሮን ከማማረር ይልቅ በችግኝ ተከላ ከተፈጥሮ ጋር የመታረቅ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ቢሊዮን ችግኞች በሕዝቡ እንክብካቤ በመፅደቃቸው የሀገራችን ልምላሜ እየተመለሰ ይገኛል። በመሆኑም አሁን የምናስመዘግበው ስኬት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ ውርስና ለበለፀገች ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚፈንጥቅ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: